መሃመድ ‹‹ ኪንግ ›› ለባሬቶ ምክትልነት ታጭቷል

የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ድንቅ ተከላካይ መሃመድ ኢብራሂም የአዲሱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ምክትልነት በፌዴሬሽኑ እይታ ውስጥ ገብቷል፡፡ በቅርቡ ከዩናይትድ ስቴትስ ተመልሶ መኖሪያውን አዲስ አበባ ያደረገው መሃመድ ለሶከር ኢትዮጵያ ‹‹ እስካሁን ስምምነት ላይ አልደረስንም፡፡ ነገር ግን ከፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ላይ ጋር እየተነጋገርን ነው ›› ብሏል፡፡

ከመሃመድ በተጨማሪ ዘንድሮ ከእግርኳስ አለም የተሰናበተው አሸናፊ ግርማም ስሙ ከምክትል አሰልጣኝነት ጋር እየተያያዘ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን እሁድ ይጫወታል

በወንድማገኝ ከበደ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን የቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታውን እሁድ ያደርጋል፡፡ ከ15 ቀናት በፊት የሲሸልስ አቻውን ከሜዳው ውጪ 2-0 አሸንፎ የተመለሰው ወጣት ቡድኑ በሜዳው ድሉን ለመድገም እንደተዘጋጀም አሰልጣኝ ወንድማገኝ ለኢቲቪ ተናግረዋል፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ በድምር ውጤት ሲሸልስን አሸንፎ ካለፈ ቀጣይ ተጋጣሚው የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ የ2014 ሴካፋ ዋንጫን ለማስተናገድ ተመረጠች

በመጪው የኢትዮጵያውያን ህዳር 2007 የሚስተናገደውን የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫን እንድታስተናግድ መመረጧን ሴካፋ አስታውቋል፡፡

የሴካፋ ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙሱንዬ እንደገለፁት ከሆነ ኢትዮጵያ የዋናው ብሄራዊ ቡድኖችን ፍልሚያ ፣ ሩዋንዳ ደግሞ የክለቦቹን ውድድር እንዲያስተናግዱ ተመርጠዋል፡፡ የሴካፋ አመራሮች ከአለም ዋንጫ መጠናቀቅ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የዝግጅት ሁኔታዎቹን ይመለከታሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በ1980 ፣ 1997 እና 1999 ይህንን ውድድር ማዘጋጀቷ አይዘነጋም፡፡

ባሬቶ ይናገራሉ

አዲሱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከሹመታቸው በኋላ ሀሳብ እና እቅዳቸውን እየተናገሩ ነው፡፡ ሰሞኑን ከሰጧቸው አስተያየቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

‹‹ በሰራሁባቸው ሃገራት ምርጥ ተጫዋቾችን አፍርቻለሁ፡፡ ስራዬን ጨርሼ ወደ ሃገሬ ስመለስ ምርጥ ተጫዋቾች በቴሌቪዥን ቀርበው በኔ እርዳታ ትልቅ ደረጃ እንደደረሱ ይመሰክራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ››

‹‹የመጣሁት ከሊዝቦን አካዳሚ ነው፡፡ ይህ አካዳሚ ከሉዊስ ፊጎ እስከ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ትልልቅ ስሞችን ያፈራ አካዳሚ ነው፡፡ ››

‹‹ አንድ ቀን ጆሴ ሞውሪንሆን አዲስ አበባ አምጥቼ ልምድ እንዲያጋራ አደርጋለሁ፡፡ ተጫዋቾችንም በአውሮፓ ክለቦች ልምምድ እንዲያደርጉ አመቻቻለሁ፡፡ ››

‹‹ ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች በአውሮፓ የአሰልጣኞች ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ ሁኔታዎችን አመቻቻለሁ፡፡ ››

‹‹ ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ባለ ክህሎት መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች እድሜያቸው ከ26 አመት በመሆኑ በወጣቶች ላይ አተኩራለሁ ››

‹‹ወርሃዊ የክፍያ መጠኑ አነስተኛ ነው፡፡ ለኔ ይመጥናል ብዬም አላምንም ፡፡ ጋና ከአመታት በፊት ወርሃዊ 30 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ትከፍለኝ እንደነበር ከግምት ሲገባ በነፃ እንደማገለግል እቆጥረዋለሁ፡፡ ››

{jcomments on}

ያጋሩ