የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና መከላከያን በሰፊ ግብ በማሸነፍ መሪዎቹን ተቀላቅሏል

 በ17ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና መከላከያን 4-0 በመርታት ከሁለት አቻ ውጤቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ውጤት አስመዝግቧል።

እንደተለመደው የአዲስ አበባ ስታድየምን ሙሉ በሙሉ በሞሉት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አስገራሚ ድባብ ታጅበው የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታውን የጀመሩት ካለፈው ሳምንት ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአንድ ተጨዋች ለውጥ በማድረግ ነበር። ኢትዮጵያ ቡና የመሀል ተከላካዩን ኤፍሬም ወንደሰንን በአምስት ቢጫ ምክንያት በማጣቱ በቦታው ኤኮ ፌቨርን ተክቶ ገብቷል ። በመከላከያዎች በኩል ደግሞ በጉዳት ምክንያት የወላይታ ድቻው ጨዋታ ያለፈው ሳሙኤል ታዬ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ሲመጣ መስፍን ኪዳኔ ወደተጠባባቂነቱ ወርዷል ። ከዚህ ውጪ ሁለቱ ተጋጣሚዎች በሚታወቁባቸው ቅርፆች ኢትዮጵያ ቡና በ 4-3-3 እንዲሁም መከላከያ በ 4-4-2 ነበር ለጨዋታው የቀረቡት ።

የቡድኖቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ መልካም እንቅስቃሴ የታየበት እና በርካታ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበሩ ። ሙከራዎቹ ከወትሮው በተለየ መልኩ ግልፅ የሆኑ እና ከግቦቹ ጥቂት ሜትሮች ላይ ይገኙ የነበሩ በመሆኑ ጨዋታው የተመልካቹን ቀልብ የያዘ እና ልብ ያንጠለጠለ ሆኖ እንዲዘልቅ አግዞታል ። የዛኑ ያህልም የተገኙት እነዚህ ዕድሎች ይሳቱ የነበሩበት መንገድ የተጋጣሚዎቹን ደካማ የአጨራረስ ብቃት እንድንመለከት ያደረገም ነበር ። መከላከያዎች የፈጠሯቸው ሁለት የመጀመሪያ አጋማሽ ዕድሎችም የዚህ ማሳያ ነበሩ ። በ8ተኛው ደቂቃ በሀይሉ ግርማ ከኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ውስጥ ከ ሀሪሰን ሄሱ ጋር ብቻ ለብቻ ተገናኝቶ ሲሞክር ቤኒናዊው ግብ ጠባቂው ያዳነበት እና በ33ኛው ደቂቃ ከቅርብ ርቀት ቴዎድሮስ በቀለ ከሳሙኤል ታዬ የተሻገረለትን ኳስ ሲመታ በግቡ የቀኝ አግዳሚ የወጣበት ኳስ ለጦሩ በቀላሉ ሊቆጠሩ ይችሉ የነበሩ ዕድሎች ነበሩ።

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጀምሮ ወደተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስ የጀመሩት ቡናማዎቹ እጅግ በቁጥር የበዙ የግብ ዕድሎችን ሲያመክኑ ተስተውሏል ። በተለይም ከግራ ክንፍ በመነሳት የመከላከያዎች የቀኝ መስመር በተደጋጋሚ እየሰበረ ይገባ የነበረው አስቻለው ግራማ በ6ተኛው ደቂቃ ላይ በራሱ ጥረት ወደ ውስጥ ይዞ በመግባት እንዲሁም በ38ተኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር ከላከለት ኳስ በመነሳት የፈጠራቸውን ዕድሎች አልተጠቀመባቸውም እንጂ በቀላሉ ወደ ጎልነት ሊቀየሩ የሚችሉ ነበሩ።

ኢትዮጽያ ቡና ወደ መሀል ሜዳ ቀርቦ ሲታይ ከነበረው የመከላከያዎች ተከላካይ መስመር ጀርባ የነበረውን ሰፊ ክፍተት በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት ሲፈትን ታይቷል ። በተለይም የቡድኑ የመስመር አጥቂዎች እና የተለመደ የማጥቃት ተሳትፎ የነበራቸው የመስመር ተከላካዮች ፈጣን እንቅስቃሴ እንዲሁም በተጋጣሚያቸው የመሀል ክፍል ላይ የበላይነት የወሰዱት የአጥቂ አማካዮቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለዚህ እንቅስቃሴው ዋነኛ መሰረቶች ነበሩ ። የአሰልጣኝ ገዛሀኝ ከተማ ቡድን ይህን ክፍተት በመጠቀም በመጀመሪያው 45 በሶስት አጋጣሚዎች በእጅጉ ወደጎል የቀረበባቸውን አጋጣሚች ማግኘት ችሏል ። በ13ተኛው ደቂቃ ከኋላ በረጅሙ ወደፊት የተላከውን ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ በግንባር ሲጨርፍለት እና ኤልያስ ሞሞ ለማስቆጠር ሞክሮ አቤል ማሞ ከግብ ክልሉ በርቀት ወጥቶ ሲመልስበት ሳኑሚ በድጋሜ አግኝቶ ቢሞክርም ያለግብ ጠባቂ ባዶውን የነበረውን የመከላከያዎች ጎል ኢላማ ማግኘት አልቻለም ። በ19ኛው እና በ32ኛው ደቂቃዎች ላይም ኢትዮጽያ ቡና በተመሳሳይ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ከግቡ አፋፍ ላይ ዕድሎችን ቢያገኝም እያሱ ታምሩ እና አህመድ ረሻድ ለማመን በሚከብድ መልኩ ስተዋቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች እነዚህን ሁሉ የግብ እድሎች ያምክኑ እንጂ የመጀመሪያውን ግማሽ 2 ለ 0 እየመሩ ነበር ወደመልበሻ ክፍል ያመሩት ። በ36ኛው ደቂቃ የአክሊሉ ዋለልኝን ግብ የሚሆን ሙከራ በሀይሉ ግርማ ከመስመር ላይ በእጁ በማምከኑ ቀይ ካርድ ተመልክቶ ሲወጣ እና 41ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ ተገኝ አስቻለው ግርማ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኙትን ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች ጋቶች ፓኖም በማስቆጠር ነበር ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገው ።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው እንደተጀመረ 47ኛው ደቂቃ ላይ ቡናዎች ከጨዋታ እንቅስቃሴ የተገኘች የመጀመሪያ ግብ አስቆጠሩ ። ግቧም ኤልያስ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ሳኑሚ በሚገባ ተቆጣጥሮ ከመታ እና አቤል ካዳነበት በኋላ በድጋሜ ሞክሮ ያስቆጠረው ነበር ። ከዚህ ጎል መገኘት በኋላ ግን ኢትዮጵያ ቡናዎች ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢወስዱም እንደመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ ዕድሎችን አልፈጠሩም ። በ75 እና 76ተኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ጊዜ በኋላ ተቀይሮ የገባው መስዑድ መሀመድ በቀኝ መስመር የተገኙ ሁለት የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ሞክሮ አቤል ማሞ አምክኖበታል ። የ90+ 3ተኛዋ የመስዑድ የረጅም ርቀት ሙከራ ግን አቤልን አልፋ በግቡ አግዳሚ ከተመለሰች በኋላ በድጋሜ በቡናዎች ቁጥጥር ስር ወደቃ በመጨረሻ በቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሀመድ አማካይነት አራተኛ ግብ ሆና ተቆጥራለች ።

የወሳኙን የተከላካይ አማካይ የበሀይሉ ግርማን በ36ተኛው ደቂቃ በቀይ መውጣት ተከትሎ ቦታውን ለመሸፈን የተጨዋች ቅያሪ ለማድረግ እስከ 58ተኛው ደቂቃ ድረስ የቆዩት መከላከያዎች ከፊት ለሚገኙትን አጥቂዎቻቸው ኳስ ለማድረስ እንዲሁም ተጋጣሚያቸው ከኳስ ጋር የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለማቋረጥ ሲቸገሩ ታይተዋል ። ከዘገየው የ58ተኛ ደቂቃ የአጉታ ኦድክ ቅያሪ በኋላም በመጠኑ አፈግፍገው በመከላከል በመጀመሪያው አጋማሽ የደረሰባቸውን ጥቃት መቀነስ የቻሉት መከላከያዎች የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ግን በቂ ዕድሎችን አላስገኘላቸውም ። በእርግጥ በ56ተኛው እና በ90+1ኛው ደቂቃ ላይ በባዬ ገዛሀኝ እና በመስፍን ኪዳኔ ጠንካራ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ። በተለይም የመስፍን ሙከራ በሀሪሰን ልዩ ብቃት ተመለሰች እንጂ ለጦሩ ማስተዛዘኛ መሆን የምትችል ነበረች ።

ጨዋታው በዚህ መልኩ በ 4 – 0 ውጤት ሲጠናቀቅ አሸናፊው ኢትዮጵያ ቡና በ 28 ነጥቦች ሁለት ደረጃዎችን አሻሽሎ ወደ አራተኛ ደረጃ ሲመጣ ከ 6 ተከታታይ አቻ ውጤቶች በኋላ ሽንፈት የገጠመው መከላከያ ከ8 ወደ 10ኛ ደረጃ ተንሸራቷል ። በቀጣዩ ሳምንት ሊጉ ቀጥሎ ሲደረግ ም ኢትዮጵያ ቡና ጎንደር ላይ በተጠባቂው ጨዋታ ፋሲል ከተማን የሚገጥም ሲሆን መከላከያ በበኩሉ የ 18ኛ ሳምንት ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍርካ ቻምፒዮንስ ሊግ ባለበት ጨዋታ ምክንያት አራፊ ይሆናል ።

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ – ኢትዮጵያ ቡና

“ጨዋታውን በማሸነፋችን ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ የኛ ዋንኛው ትኩረታችን ከፊታችን ያሉትን ጨዋታች እያሸነፍን መሄድ ነው፡፡ ይህን ማሳካት ከቻልን ወደ ዋንጫ የምናደርገውን ጉዞ ማሳመር እንችላለን፡፡”

*የመከላከያ ዋናም ሆነ ምክትል አሰልጣኝ ለሚዲያ አካላት አስተያየታቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡

Leave a Reply