ፕሪምየር ሊጉ በጎል የተንበሸበሸበትን ልዩ ሳምንት አሳልፏል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተካሂዶ 6 ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀዋል፡፡ ሲዳማ ቡና ወደ መሪው ሲጠጋ ቡና እና ሀዋሳ በሰፊ ጎል ልዩነት ተጋጣሚዎቻቸውን ረምርመዋል፡፡ በጎል ድርቅ ተመትቶ የሰነበተው ሊጉም በዚህ ሳምንት በተደረጉ 8 ጨዋታዎች 24 ግቦች ተስተናግዶበት አልፏል፡፡


ወላይታ ድቻ 2-1 ፋሲል ከተማ

ሶዶ ላይ ሁለቱ የደጋፊ ሀብታሞችን ያገናኘው ጨዋታ በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ተመጣጣኝ ፍክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ የጫወታ ክፍለ ጊዜ የፋሲል ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ የጭንቅላት ህመም አጋጥምት በ20ኛው ደቂቃ ጨዋታውን አቋርጦ ወደ ሆስፒታል አምርቷል፡፡ በዚህ የጨዋታ አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡

በ23ኛው ደቂቃ ፈቱዲን ጀማል ያቀበለውን የቀኝ ተከላካዩ አናጋው ባደግ ከ16:50 ውጭ አክርሮ መትቶ ድቻን ቀዳሚ አድርጎ የመጀመሪያው አጋማሽ በድቻ መሪነት ተጠናቋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከተማ ወላይታ ዲቻን ተጭኖ የተጫወተ ሲሆን አሰልጣኝ ዘማርያም ህክምናውን ጨርሶ በ50ኛው ደቂቃ ወደ ሜዳ ተመልሶ ክለቡን መርቷል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ የፋሲል ከተማው ቶጓዊ አጥቂ ኤዶም ሆውሶሮቪ ከአብዱራህማን ሙባረክ የተቀበለውን ኳስ አስቆጥሮ ፋሲል አቻ ቢያደርግም ከደቂቃዎች በኃላ ከአርባ ምንጭ ከተማ ዲቻን የተቀላቀለው ተመስገን ዱባ ከያሬድ ዳዊት የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት በመጀመርያ ጨዋታው ድቻን ወደ ድል የመራች ወሳኝ ጎል አስቆጥሯል፡፡

ከጨዋታው በኃላ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ መሣይ ተፈሪ በጥንቃቄ ተጫውተው እንደዳሸነፉ ሲገልጹ የፋሲል ከተማው ዘማርያም ወ/ጊዩርጊስ ሜዳው ለጨዋታ ምቹ አለመሆኑ በውጤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩን ገልጸው በድቻ ደጋፊዎች የአደጋገፍ ሁኔታ ደስ እንደተሰኙ ተናግረዋል፡፡


ጅማ አባ ቡና 1-0 አአ ከተማ

ጅማ ላይ አዲስ አበባ ከተማን የገጠመው ጅማ አባቡና ወርቃማ ሶስት ነጥብ አሳክቷል፡፡ በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ባለሜዳዎቹ ጅማ አባቡናዎች የተሻሉ ሆነው የታዩ ሲሆን በኪዳኔ አሰፋ እና አሜ መሀመድ አማካይነት የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ፈጥረዋል፡፡  በ10ኛው ደቂቃ ተከላካዩ ቢያድግልኝ ኤልያስ ወደ ግብ የሞከረውና የግቡ ቋሚ የመለሰበት አባቡናን መሪ ሚያደርግ አጋጣሚ ነበር፡፡ በ19ኛው ደቂቃ የመስመር ተጫዋቹ ዳዊት ተፈራ ያሻማውን ኪዳኔ አሰፋ ተጠቅሞበት የጨዋታውን ልዩነት ፈጣሪ ጎል አስቆጥሯል፡፡


ወልድያ 1-1 አርባምንጭ ከተማ

ወልድያ በመሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም አርባምንጭን አስተናግዶ 1-1 አቻ ተለያይቷል፡፡ በዚህ ሳምንት በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ብቸኛ ጨዋታ ሆኖም ተመዝግቧል፡፡

በርካታ ተመልካች እና ያማረ የደጋፊዎች ድባብ በነበረው ጨዋታ ደጋፊውን ቁጭ ብድግ የሚያደርግ እና በሁለቱም በኩል ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው አርባ ምንጮች ቢሆኑም የሙከራ የበላይነት ግን የወልድያዎች ነበር።

በ4ኛው ደቂቃ ኤሪክ በአንድ ሁለት ቅብብል ከመስመር ወደ መሀል ይዞት የገባውን ኳስ አክርሮ መትቶ አንተነህ መሳ ያዳነበት በወልድያ በኩል የመጀመሪያ አደገኛ ሙከራ ነበር።

ጨዋታው በፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ የቀጠለ ሲሆን በ26ኛው ደቂቃ ወንድሜነህ በጥሩ ሁኔታ ተቀባብሎ የመታው ኳስ በጎሉ በላይ ወጥቷል። 
በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት አመለ ሚልኪያስ ከቢሌንጌ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የሞከረውን ግብ ጠባቂው በግሩም ብቃት ሲያድነው አንዱአለም ንጉሴ ከመስመር ወደ ጎል አክርሮ በመምታት ሞክሮ አንተነህ ያወጣበት በሁለቱም በኩል የተደረጉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የጨዋታ የበላይነቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ወልድያ ያደላ ሲሆን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በግብ ሞከራዎች የታጀበ ነበር። አርባ ምንጮችም ወልድያ የሰሯቸውን ስህተቶች ለመጠቀም እና በመልሶ ማጥቃት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ታይቶበታል።

በ48ኛው ደቂቃ በግራ መስመር በኩል ታዬ እና ኤሪክ ኮልማን ተቀባብለው ታዬ ያሻማውን ኳስ አቤጋ አስቆጥሮ ወልድያን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል። የወልድያ መሪነት ግን ለ6 ደቂቃዎች ነበር የዘለቀው፡፡ በ54ኛው ደቂቃ በወልድያ ተካላካዮች እና ቢሌንጌ መካከል በተፈጠረ ያለመናበብ ችግር ተጠቅሞ አመለ ሚልኪያስ አርባምንጭ ከተማን አቻ አድርጓል፡፡ 

ከግቦቹ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች የግብ እድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ64ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ኳስ ሞክሮ ቢሌንጌ ያዳነበት በ66ኛው ደቂቃ ደግሞ በቀጥታ የመታውን ቅጣት ምት የግቡ ቋሚ የመለሰበት በአርባምንጭ በኩል የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡ 

በወልድያ በኩል በ71ኛው ደቂቃ ታዬ እና በ77ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ሞክረው የግቡ አግዳሚ የመለሰባቸው ኳሶች የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ፣ ኢትዮጵያ ቡና መከላከያን 4-0 በሆነ ተመሳሳይ ውጤት ሲረቱ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድሬዳዋ ከተማን 3-1 ፣ ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን 1-0 አሸንፈዋል፡፡  ትላንት በተደረገ ጨዋታ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢትን 3-2 በማሸነፍ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል፡፡


የጨዋታ ሪፖርቶችን ከዚህ በታች ያገኟቸዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 ደደቢት 


ሲዳማ ቡና 1-0 አዳማ ከተማ 


ሀዋሳ ከተማ 4-0 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ


ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-1 ድሬዳዋ ከተማ


ኢትዮጵያ ቡና 4-0 መከላከያ 


Leave a Reply