የኢትየጵያ ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የ1ኛው ዙር ውድድር አፈፃፀም ሪፖርት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ እና የብሔራዊ ውድድር የሊግ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አሊሚራህ መሀመድ ፣ የፌዴሬሽኑ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ፣ የሊግ ኮሚቴ ፣ የዳኞች ኮሚቴ ፣ የዲስፕሊን ኮሚቴ እና የክለብ ተወካዮች በተገኙበት ዛሬ የካቲት 27 ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ በኢትዮዽያ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ተካሄዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ መሰረት ውድድሩን የሚመሩት ሦስቱ አካላት ሊግ ኮሚቴ ፣ የዳኞች ኮሚቴ ፣ ዲስፕሊን ኮሚቴ እና ፀጥታ አካላት ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የ1ኛው ዙር አፈፃፀም ሪፖርት በየቅደም ተከተላቸው በውድድሩ ላይ የነበሩ ጠንካራ ጎን እና ደካማ ጎኖችን ዘርዝረዋል፡፡ ውድድሩ በኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ለመጀመርያ ጊዜ እንደ መዘጋጀቱ የተገኙ ውጤቶችን በማቅረብ በቀጣይ በሁለተኛው ዙር የውድድር መርሐ ግብር ላይ ሊወሰዱ የሚገቡ የፍትሔ ዕርምጃዎች ይገባል ያሉትን ሀሳቦች በዝርዝር አቅርበዋል።

በመቀጠል የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት ተካሂዶ ከሻይ እረፍት መልስ በቀረቡት ሪፖርቶች ዙሪያ የክለብ ተወካዮች ዋና ዋና ያሏቸውን ነጥቦች አንስተዋል፡፡ እኛም ጠቅለል አድርገን እንሚከተለው አቅርበነዋል፡-

– የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውድድሩን ወደ ራሱ ባለቤትነት ሲያመጣው አስቀድሞ ምንም አይነት ዝግጅት አላደረገበትም። የአዲስ አበበ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተሳካ የውድድር ፕሮግራም ምቹ በሆነ ሜዳ በበርካታ ተመልካች ፊት ነበር የሚካሄደው ዘንድሮ ተቀዛቅዟል፡፡

– ለውድድሩ አስፈላጊ የሚባሉ ሜዳዎች ምቹ አይደሉም፡፡ ተመልካች አልባ ነው። የህክምና ባለሙያ እና ኳሶች እየቀረቡበት አይደለምና ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል ።

– የዕድሜ ጉዳይ ሊጤንበት ይገባል፡፡ እርግጥ ነው ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ቢሆንም አሁንም ለጊዜያዊ ውጤት ቅድሚያ በመስጠት ያለ ዕድሜያቸው የሚያጫውቱ አሉ፡፡ ይህ ቢሻሻል ምክንያቱም ትክክለኛ የሆኑ ተተኪዎችን በዚህ ሁኔታ ማግኘት አይቻልም።

– የሚዲያ ሽፋን አነስተኛ ነው። ፌዴሬሽኑ ራሱ ትኩረት አልሰጠውም፡፡ አንዳቸውም የፌዴሬሽኑ አመራሮች ውድድሮችን እየተከታተሉ አይደለም፡፡ በመሆኑም አላማችን ታዳጊዎችን ማፍራት ከሆነ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል፡፡

በቀረቡት አስተያየቶች ላይ የፌዴሬሽኑ የተለያዩ ኮሚቴዎች ምላሽ የተሰጠበት ሲሆን በዋናነት ክለቦች በራሳቸው በኩል ሊቀረፉ የሚገቡ ችግሮችን ወደ ፌዴሬሽኑ ባያመጡና እርስ በእርስ በመነጋገር ቢፈቱ የተሻለ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዳኞች እና በኮሚሽነር በኩል ችግሮች እንዳሉ ያመነው ፌዴሬሽኑ ለማስተካከል እንደሚሰራ አሳውቋል፡፡ ከዕድሜ ጋር በተያያዘ ዘንድሮ ከህክምና ቡድኑ ጠንካራ ስራ ተሰርቷል ፤ ብዙ ለውጦችም መጥተዋል፡፡ ያም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ችግሩ ተፈትቷል ብሎ ፌዴሬሽኑ እንደማያምንና በቀጣይ እንደሚሰራ ገልፆ በተለይ ግን ጊዜያዊ ውጤት የምትፈልጉ ክለቦች እንደ ሀገር የምታስቡ ከሆነ ልታስተካክሉ ይገባል የሚል አስተያየት ተሰጥቷል።

በቀጣይ ወድድሩ በጥሩ ሁኔታ እንዲቀጥል ችግሮችን አስተካክሎ የሚቀርብ መሆኑን ፌዴሬሽኑ አሳውቆ የዕለቱ መርሐ ግብር ፍፃሜ ሆኗል።

1 Comment

  1. Dear Ethio Soccer:- Ethiopian Insurance Corporation has its own logo.Please use the logo for the U17 and U20 Foot Ball teams.You are posting news(tables,fixtures)about them without attaching the logo.Its available on Ethiopian Insurance Corporation website.
    Thank You in advance

Leave a Reply