የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ምክንያት ለአንድ ሳምንት ተቋርጦ ተመልሷል፡፡ ደደቢት እና አዳማ ከተማ በግስጋሴያቸው ሲቀጥሉ ኤሌክትሪክም አሸንፏል፡፡
በ8፡00 ጥረትን አበበ ቢቂላ ላይ ያስተናገደው ደደቢት እጅግ ፍፁም ከሆነ የጨዋታ የበላይነት ጋር 5-0 አሸንፏል፡፡ ለደደቢት ግቦቹን ልማደኛዋ ሎዛ አበራ ሁለት እንዲሁም ሰናይት ቦጋለ ፣ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ እና አልፊያ ጃርሶ አንድ አንድ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል፡፡
በደደቢት በኩል ሰናይት ቦጋለ እና ብሩክታዊት ግርማ ጥሩ ሆነው በዋሉበት ጨዋታ በዘንድሮው የውድድር አመት ከግብ ጋር የተጣላችው አጥቂዋ ሠናይት ባሩዳ አሁንም ከግብ ጋር መታረቅ አልቻለችም ፤ እንዳለመታደል ሆኖ በዚሁ ጨዋታ ላይም ግብ ልታስቆጥርባቸው የምትችልባቸውን ሁለት ሙከራዎች የግቡ አግዳሚ መልሶባታል፡፡
በአንጻሩ ጥረቶች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ መንቀሳቀስ ቢችሉም በሂደት ተዳክመው ተስተውለዋል ፤ በዚህም ሠርካዲስ ጉታ ከቆሙ ኳሳች ከሞከረቻቸው ሁለት ኳሶች በስተቀር በክፍት ጨዋታ ወደ ደደቢት የግብ ክልል መድረስ ባለመቻላቸው የደደቢትዋ ግብ ጠባቂ ገነት አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጨዋታውን እንደ ተመልካች ልትታደም ተገዳለች፡፡
ቀጥሎ ከምድብ ለ የተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ልደታ ጨዋታ ከመጀመሪያው በተሻለ ተመጣጣኝ እና ማራኪ ፉክክር ታይቶበት 1-1 ተጠናቋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙአየሁ ታደሠ ባስቆጠረችው ግብ ሲመሩ ቢቆዩም ልደታ ክ/ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ተቀይራ ወደ ሜዳ በገባችው ቤቴል በቀለ የአቻነት ግብ 1-1 ሊለያዩ ችለዋል፡፡
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ቦሌ ክፍለ ከተማን የገጠመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-0 አሸንፏል፡፡ በአካል ብቃትም ሆነ እድሎችን በአግባቡ በመጠቀም የተሻሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ገና በመጀመርያው ደቂቃ የፍጹም ቅጣት ምት ቢያገኙም አይናለም ጸጋዬ የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ በቀላሉ መልሳዋለች፡፡ ሆኖም አይናለም በ14ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥራ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች፡፡ በ27ኛው ደቂቃ ደግሞ አለምነሽ ገረመው ሁለተኛውን አክላለች፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ቦሌዎች የተሻለ መንቀሳቀስ እና ኳስ መቆጣጠር ቢችሉም የተሳካ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በኤሌክትሪክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
11:30 ላይ ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን አስተናግዶ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩበት ግቦች 3-2 ተሸንፏል፡፡ ጠንካራ ፣ አዝናኝ እና ፈታኝ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ አዳማ ከተማዎች 2-0 ከመመራት አንሰራርተው ድል አስመዝግበዋል፡፡
በመጀመርያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ እንቅስቃሴ በማሳየት በ12ኛው ደቂቃ ቁምነገር ካሳሁን ባስቆጠረችው ግብ ቀዳሚ ሆኖ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል፡፡ ከእረፍት መልስ አዳማ ከተማ የአቻነተ ጎል ፍለጋ ተጭኖ ሲጫወት ቡና በመልሶ ማጥቃት ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር፡፡ በዚህም 51ኛው ደቂቃ ላይ ሀና አበበ ቡና 2-0 መምራት የሚችልበትን ጎል አስቆጥራለች፡፡
ከጎሉ በኋላ ሙሉ ለሙሉ የአዳማ ከተማ የበላይነት የታየ ሲሆን ቀሪዎቹ 35 ደቂቃዎችም በቡና የሜዳ አጋማሽ ላይ አመዝኖ ተስተውሏል፡፡
በ60ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ ሲመለስ አምበሏ ገነት ኃይሉ በቀጥታ መትታ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት በመለወጥ አዳማን ወደ ጨዋታው መልሳዋለች፡፡ አዳማዎች ይበልጥ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለው በ85ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ቅድስት አባይነህ በቡና የግብ ክልል ውስጥ ናርዶስ ጌትነትን ጠልፋ በመጣሏ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሴናፍ ዋቁማ አስቆጥራ አዳማን አቻ አድርጋለች፡፡ ፍጹም ቅጣት ምት ያስገኘችው ናርዶስ ግን ከባድ ጉዳት በማስተናገዷ ተቀይራ ወጥታለች፡፡
የጨዋታው መደበኛ ክፍለጊዜ መገባደጃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በእለቱ ድንቅ የነበረችው አስካለ ገብረጻዲቅ በግምባሯ በመግጨት አዳማን ከተመሪነት ወደ አሸናፊነት ማሸጋገር ችላለች፡፡ አስካለ የገጨችው ኳስ ጥንካሬ በሴቶች እግርኳስ እምብዛም ያልተለመደና ግብ ጠባቂዋ ለመመለስ እድል ያልሰጠ ነበር፡፡
ምድብ ሀ
[table id=231 /]
[league_table 18073]
ምድብ ለ
[table id=239 /]
[league_table 18083]