ከኢትዮጵያ ውጪ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እግርኳስን የሚያጫወቱ ተጫዋቾች አሉ፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም በተለያዩ ግዜያት ኢትዮጵያዊያን እና የዘር ሃረጋቸው ከኢትዮጵያ የሚመዘዙትን ተጫዋቾች ስታስተዋውቅ ቆይታለች፡፡ በዛሬው ጽሁፍም ከወደ አውስትራሊያ አንድ ኢትዮጵያዊ እናስዋውቃችኀለን፡፡
ትውልዱ አዲስ አበባ አፍንጮ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ ነው ፍራኦል ሊካሳ፡፡ የ27 ዓመቱ ፍራኦል ለ10 ዓመታት ካደገባት ሃገሩ ኢትዮጵያን ለቆ ኑሮውን በሜልቦርን አውስትራሊያ ካደረገ ዓመታት አልፈውታል፡፡ በአውስትራሊያ ናሽናል ፕሪምየር ሊግ ቪክቶሪያ 2 ለኑናዋዲንግ ሲቲ የሚጫወተው የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ከእግርኳስ ተጫዋችነቱ ባሻገር የስፖርት ሳይንስ ተማሪ ነው፡፡ ኑናዋዲንግ ሲቲ በአውስትራሊያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አንጄ ፖስትኮግሉ አማካሪነት የሚመራ ክለብ ነው፡፡ ናሽናል ፕሪምየር ሊግ ቪክቶሪያ 2 በአውስትራሊ የሊግ አደረጃጀት ከኤ ሊግ እና ቪክቶሪያ 1 ሊግ ቀጥሎ የሚገኝ ሊግ ነው፡፡ ፍራኦል በተደራቢ አጥቂነት፣ የመስመር አጥቂ እና የፊት አጥቂ ሆኖ መጫወት ይችላል፡፡
ፍራኦል ስለእግርኳስ ህይወቱ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያው ኦምና ታደለ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ፡ ከኢትዮጵያ ከወጣህ በኃላ እግርኳስን በአካዳሚ በመጫወት ነው የጀመርከው ወይስ የተለመደው ዓይነት አካሄድ ነበረህ?
ፍራኦል ሊካሳ፡ እውነት ለመናገር ወደ እግርኳሱ የተሳብኩት አውስትራሊያ ካቀናው በኃላ ነው፡፡ በ11 ዓመቴ ለትምህርት ቤት ክለብ በመጫወት ነው የመጀመሪያ አጀማመሬ፡፡ በመቀጠል በታዳጊ ክለቦች ውስጥ ታቅፌ ከ13 እና ከ14 ዓመት ብድኖች ውስጥ ታቅፌ አስፈላጊውን የእግርኳስ ትምህርቶች ቀስሚያለው፡፡ ከ13 ዓመት ቡድን ውስጥ በከበርኩበት ወቅት ክልሌን ቪክቶሪያን ወክዬ በአውስትራሊያ የታዳጊዎች ውድድር ላይ ተሳትፎ አድርጊያለው፡፡ ሳውዝስፕሪንግቪል ለተባለ ክለብ ነው እግርኳስን መጫወት የጀመርኩት፡፡
ከዚህ ቀደም ከማል ኢብራሂም እና ቴዎድሮስ ያቢዮን በጠየቅንበት ወቅት በአውስትራሊያ የታዳጊዎች ማሰልጠኛዎች ስልጠና መውሰዳቸውን ነግረውናል፡፡ ወደ ኤ ሊግም ለማቅናት እንደጠቀማቸው አያይዘው ገልፀዋል፡፡ በአንተ በኩል ያለውስ ጉዳይ ምን ይመስላል?
አዎ ከማል እና ቴዲ በታዳጊዎች ሰልጠና ውስጥ ታቅፈው ነው እስከዋናው ለግ ማምራት የቻሉት፡፡ እኔ በኤ ሊግ መጫወት ባልችልም አካሄዴ ከነሱ አይለይም በ17 ዓመቴ ነበር በምጫወትበት ክለብ ዋናው ቡድን መቀላቀል የቻልኩት፡፡
አብዛኛውን ግዜ ኢትዮጵያዊያን ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ትምህርት እንዲያዘነብሉ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ በኩል እግርኳስን መጫወት መምረጥህ በወላጆችህ ድጋፍ አግኝቷል?
አዎ ኢትዮጵያዊያን ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ትምህርተ ቢያዘነብሉ ደስ ይሰኛሉ፡፡ ይህ ነገር እኔም ላይ እንደዛው ነው ያጋጠመኝ ነበር የኃላኃላ በማሳየው ነገር እና ውጤታማ እየሆንኩ ስመጣ ጫናው ቀሎልኛል፡፡ አሁን ላይ ለስራዬ አክብሮት እና ድጋፍ አላቸው፡፡
ከኑናዋዲንግ ሲቲ ጋር በ2016 ለመለያየት ተቃርበህ ነበር…
ከአሁን ክለቤ ጋር ለመለያየት ተቃርቤ ነበር፡፡ በህዳር 2016 አንድ ዩአይምኤም የተባለ የማሌዢያ ክለብ ግልጋሎቴን ለማግኘት ከወኪሌ ጋር ድርድር ጀምሮ ነበር፡፡ በወቅቱ የእግር ጉዳት ላይ ስለነበርኩ ወደ ክለቡ የማደርገው ጉዞ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ አሁን ላይ ከጥር ወር ጀምሮ በኑናዋዲንግ ሲቲ ቆይታዬን እስከአመቱ መጨረሻ ማድረግን መርጫለው፡፡ የሊግ ውድድር ከተጀመረ ሳምንታትን አስቆጥረናል፡፡ ከፊታችን የሊግ እንዲሁም የጥሎ ማለፍ ዋንዓ ጨዋታዎች አሉብን፡፡ በነዚህ ጨዋታዎች ከክለቤ ጋር የተሻለ ነገር ማሳየት እፈልጋለው፡፡ አሁን ላይም ከታይላንድ እና ማሌዢያ ክለቦች ጋር ግንኙነት ፈጥረን ወደ ክለቦቹ የማመራበትን መንገድ እያመቻቸው ነው፡፡ በግንቦት ወር ላይ ተስፋ አድርጋለው ከአውስትራሊያ ውጪ እንደምጫወት፡፡
ከአውስትራሊያ አንደኛ ይሁን ሁለተኛ ዲቪዚዮን ወደ ኤ ሊግ እምብዛም ተጫዋቾች ሲፈርሙ አይታይም፡፡ ከዚህ ቀደም በአንደኛ ዲቪዚዮን የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች የነበረው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ከማል ኢብራሂም ባለው ነባራዊ ሁኔታ እንደሚከፋ ተናግሯል፡፡ ለአፍሪካዊያን ተጫዋቾች ነገሩ እንደሚከብድ ይነገራል፡፡ አንተም ከአውስትራሊያ ውጪ ለመጫወት የፈረግከው ለዚህ ነው ወይም ሌላ ምክንያት አለ?
ኤ ሊግ ድንቅ የውድድር መድረክ ነው፡፡ ወደ ስርዓቱ ገባህ አንዴ እዛው ወደ ተለያዩ ክለቦች እያመራህ ለረጅም ግዜ መጫወት ትችላለህ፡፡ አንዴ ከሊግ ከወጣህ ግን ነገሮች ከባድ ናቸው፡፡ ቴዲ እና ከማልም የዚሁ ችግር ተጋፋጭ ከሆኑ መካከል ናቸው፡፡ በ2004 ኤ ሊግ ከተመሰረተ በኃላ ክለቦች ሶስት ትልቅ ስም ያላቸው ተጫዋቾች ክለቦች መያዝ አለባቸው፡፡ ይህንን ለማድረግ የፋይናንስ አቅምህ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ሜልቦርን ሲቲ (የከማል ኢብራሂም የቀድሞ ክለብ) ድቪድ ቪያን አስፈርሞ ነበር፡፡ በቀሪዎቹ ቦታዎች ከታች ካሉ ሊጎች ችሎታ ተጫዋቾች ከማስፈረም ይልቅ በሊጉ የቆዩ ተጫዋቾችን ማስፈረም ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ የተወሰኑ ቦታዎችን ለወጣት ቡድን ተጫዋቾች ይሰጣሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ወደ ኤ ሊግ ለመምጣት ነገሮች አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡ እንደአፍሪካዊ ተጫዋች ጥቁር መሆን እራሱን የቻለ አሉታዊም አዎንታዊም ጎኖች አሉት በእርግጥ፡፡ አሁን ላይ 10 ተሳታፊ ክለቦች ያሉት ኤ ሊግ ላይ መውጣት እና መውረድ አሁን ላይ የለም፡፡ ቢሆንም አደረጃጀቱን በማሻሻል ብዙ ክለቦች ተሳታፊ ለማድረግ ጅማሮዎች ስላሉ ተጫዋቾች ወደፊት እድል የሚያገኙበት መንገድ የሚከፈት ይመስለኛል፡፡
የትውልድ ሃገርን የመወከል ፍላጎት በአንተ በኩል አለ?
ይህ የአጭር ግዜ እቅዴ ነው፡፡ የህይወቴን የመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታትን ያሳለፍኩት በኢትዮጵያ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ ስለሃገሬ ያለትን ባህል እና ጥሩ ነገሮች እያወቅኩ እንዳድግ ስላደረጉኝ ብሄራዊ ቡድኑ የመረዳት ፍላጎት እንዲያድርብኝ አድርጓል፡፡ ከሃገር ውጪ የሚጫወቱ ብዙ ጥሩ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች አሉ ሃገራቸውን መወከል የሚፈልጉ ግን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ያለንን ብቃት ለመመልከት እንኳን የዘረጋው አሳታፊ ስርዓት አለመኖሩ ፍላጎታችንን ህልም ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት በዚህ እራሳቸው እየጠቀሙ ነው፡፡ አሁን ላይ ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ከሃገር ውስጥ ጋር በመቀላቀል የተሻለ ቡድን እየገነቡ እያየን ነው፡፡
ውጪ የሚጫወቱ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች የተለየ ነገር እያሳዩን ስላልሆነ መመረጥ የለባቸውም የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ….
መመጠናቸው እና አለመመጠናቸውን ለማወቅ በጣም ቀላል ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ልስጥህ አንድ ላይቤሪያዊ የክለብ አጋር ነበረኝ፡፡ የላይቤሪያ ፌድሬሽን ጥሪ አድርጎለት ብሄራዊ ቡድኑን ወከል ችሏል፡፡ አሁን ላይም በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ብሄራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገለት በአቋም መለኪያ መጫወታዎች ላይ ነው፡፡ የቡድኑ አሰልጣኞች በአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ያለውን አቋም አዩ ከእዛ በኃላ ያለው ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ነገር ስታደርግ አይስተዋልም፡፡ ሁሉም በውጪ የሚጫወት ኢትዮጵያዊ ተጫዋች አይመጥንም ግን የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን በማዘጋጀት የሚመጥኑ ተጫዋቾችን ማግኘት ይቻላል፡፡ ያለን ብቃት የተድረስ እንደሆነ ሳይታወቅ በጥቅሉ አይመጥኑም ማለት አግባብነት የለውም፡፡ በወዳጅነት ጨዋታ እንታይ ከዛ በኃላ አሰልጣኞቹ የፈለጉትን ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ የተጫዋቾችን ሲቪ፣ የእንቅስቃሴ ምስሎችን መሰብሰብ ፌድሬሽኑ ነገሮች ለማጣራት ቀላል ያደርግለታል፡፡ ሁላችንም ፍላጎት ኢትዮጵያ የተሻለ ቡድን እንዲኖራን እስከሆነ ፌድሬሽኑ እቅድ ይዞ ቢያስብበት ጥሩ ነው እላለው፡፡
የኑናዋዲንግ ሲቲ ቆይታ ምን ይመስላል?
በጣም ጥሩ ቆይታ ነው ያለኝ፡፡ የምንከተለው የእግርኳስ ፍልስፍና ኳስን በመቆጣጠር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የባርሴሎናን የአጨዋወት ስልት ለመቅዳት ክለቡ ይሞክራል፡፡ የሚረዳው በአውስታራሊያ እግርኳስ ትልቅ ስም ያለው አንጄ ነው፡፡ ለመጫወት ጥሩ ቦታ ኑናዋዲንግ፡፡ በአውስታራሊ የግሪክ፣ ክሮሺያ፣ ሰርቢያ እና ጣሊያን ማህበረሰብ ቡድኖች በስፋት ይገኛሉ፡፡ ብዙ ገንዘብን በቡድኖቹ ላይ ፈሰስ ያደርጋሉ፡፡ ኑናዋዲንግም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ አስቀድሜ እንደገልፅኩት ወደ በሊግ እና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ከ30 በላይ ጨዋታዎች አሉብን፡፡ በቆይታዬ ክለብን ወደ ተሻለ ቦታ መውሰድ ነው አላማዬ፡፡