ቅዱስ ጊዮርጊስ ሬኔ ፌለርን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ሾመ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሰናባቹ አሰልጣኝ ማርተ ኑይን ተክቶ የሚያሰለጥነውን ጊዜያዊ አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡ ሆላንዳዊው የቀድሞ የኤፒአር እና የኤርትራ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሬኔ ፌለር ፈረሰኞቹን እስከ ውድድር ዘመኑ ማብቂያ ድረስ ይመራሉ፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ በምስራቅ አፍሪካ የካበተ ልምድ ያላቸው አሰልጣኝ ሲሆኑ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለመምጣታቸው የማርት ኑይ አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስን በዚህ የውድድር ዘመን የተረከቡት ሆላንዳዊው አሰልጣኝ ማርት ኑይ የታንዛንያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እንዲሆኑ በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ጥሪ በቀረበላቸው መሰረት መስማማታቸው ይታወሳል፡፡ አዲሱ የታይፋን ስታርስ አሰልጣኝ ዛሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳሽን ቢራን የሚያስተናግድበትን ፍልሚያ መርተው በዛው ወደ ዳሬሰላም ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፕሪሚየር ሊግ

ትላንት በተካሄደው የ16ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ብቸኛ መርሃ ግብር መብራት ኃይል ወላይታ ድቻን 1-0 አሸንፏል፡፡ ለመብራት ኃይል ብቸኛዋን ግብ ከመረብ ያሳረፈው ተከላካዩ አዎዪኒ ሚካኤል በግንባሩ በመግጨት ነው፡፡ ድሉን ተከትሎ መብራት ኃይል ደረጃውን በአንድ አሻሽሎ 11ኛ ሲቀመጥ ተሸናፊው ወላይታ ድቻ ደግሞ አንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ሊጉ ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ሐረር ላይ ሐረር ሲቲ ከ መከላከያ ፣ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ከ ደደቢት ፣ ይርጋለም ላይ ዘንድሮ በሜዳው ሽንፈት ያልቀመሰው ሲዳማ ቡና ከ ሀዋሳ ከነማ ፣ አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ከ ኢትዮጵያ መድን አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ዳሽን ቢራ በተመሳሳይ በ9፡00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የዳሽን ቢራ ጨዋታን ተከትሎ በ11፡30 ኢትዮፕ ቡና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይጫወታሉ፡፡

{jcomments on}

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *