የ2009 ኮፓ ኮካ ኮላ በመጋቢት ወር አጋማሽ ይጀመራል

የ2009 ኮፓ ኮካ ኮላ ከ15 ዓመት በታች ውድድር በመጋቢት ወር አጋማሽ ይጀመራል፡፡ ከ36,000 በላይ ተማሪዎች የሚሳተፉበት የትምህርት ቤት ውድድር በቅድሚያ ሲካሄድ የተሻለ ተሰጥኦ የታየባቸው ተጫዋቾች ተመርጠው በየክልሎቻቸው ውድድር ያደርጋሉ፡፡ በመቀጠልም ክልላቸውን/የከተማ መስተዳድራቸውን ወክለው በሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡ ከማጠቃለያው ላይ የሚመረጡ ታዳጊዎችም ወደ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ይገባሉ፡፡

የ2009 ውድድርን በይፋ ለማስጀመር ሀሙስ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ ኮካ ኮላ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የክልል የስፖርት ቢሮዎች እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የውድድሩ ባለድርሻ አካላት መሆናቸው በመግለጫው ሲጠቀስ የፓናል ውይይትም የስነ ስርዓቱ አካል ነበር፡፡

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ጁነይዲ ባሻ በታዳጊዎች ላይ መስራት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ “ትልቁ ነገር መሰራት ያለበት ወጣቶች ላይ ነው እያልን ብዙ ግዜ እንናገራለን፡፡ በታዋቂ ሰዎችም ይሁን እግርኳሱን እንዲያድግ በሚፈልጉ እዚም ሃገር ሆነ ከሃገር ውጪ ማንኛውም ሰው የሚያስበው በወጣት ላይ መስራት ነው፡፡ በእግርኳስ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የስራ መስክ በወጣት ላይ መስራት ያዋጣል ፤ ኪሳራ የለውም፡፡ ፌድሬሽኑ ካስቀመጣቸው አምስት ዋና ዋና ስትራቴጂዎች መካከል ልማት ላይ መስራት ነው፡፡ በእድሜ እና በውድድር ደረጃ እንደምታውቁት በ17 እና 20 ዓመት በታች እየሰራን ነው፡፡ ተማሪ ደግሞ በበጋው ትምህርት ላይ ስለሆነ ማወዳደር አይቻልም፡፡ የዛሬ እግርኳስ እውቀትን ስለሚፈልግ ክረምት ላይ እና ወደ መጨረሻ አከባቢ ውድድሮችን እንዲያደርጉ እያደረግን ነው በየአከባቢያቸው፡፡ ትምህርት ቤት ሲዘጋ አወዳድረን የተሻሉ ተስጥኦ ያላቸውን ተጫዋቾች ለማምጣት ነው ግባችን፡፡ ኮካ ኮላ በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም በአፍሪካም ላይም ይሰራል፡፡ ከዚህ ቀደም ምንም አልተጠቀምንበትም ነበር፡፡ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ መለስተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እናዳርግ ነበር፡፡ አሁን ግን ሙሉ ሃገሩን ወደ 1000 ትምህርት ቤቶች እና 36 ሺህ ተማሪዎችን ለማሳተፍ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የኮካ ኮላ የኢትዮጵያ ሃላፊ ኪንግ ኦሪ ማቻሪያ በበኩላቸው ብዙ ታዳጊዎች በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ፍቃደኝነታቸው ማሳየታቸው የመነሳሳት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ “የክልል እና አካባቢ መስተዳድሮች ለሰጡን ድጋፍ እና የታዳጊዎች ስልጠና ስኬታማ እንዲሆን ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች በዘንድሮው አመት ለመወዳደር ፍቃደኛ መሆናቸው በጣም አስደስቶናል፡፡ ኮፓ ኮካ ኮላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተስጥኦዎችን እውቅና ለመስጠት በድርጅታችን የሚዘጋጅ ነው፡፡ የምናውለው መዋለ ንዋይ አቅም እና ተስጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች ለማጎልበት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በሚደረገው ጥረት ላይ የሚረዳ ነው፡፡”

የኮካ ኮላ ብራንድ ሃላፊ ወ/ሪት ትግስት ጌቱ በበኩሏ በአለም እግርኳስ ስመጥር የሆኑ ተጫዋቾች በኮፓ ኮካ ኮላ ስር ማለፋቸውን እና ኢትዮጵያም በዚሁ መልኩ ጥሩ ተጫዋቾችን ለማግኘት ውድድሩ ይረዳታል ብላለች፡፡ “በአለም ላይ ከፍተኛ አድናቆት ያፈሩ እንደሊዮኔል ሜሲ ያሉ ተጫዋቾች የወጡበት በኮካ ኮላ የእግርኳስ መድረክ ነው፡፡ በኢትዮጵያም እንደሩጫው ሁሉ የሃገራችንን ስም በአለም መድረክ የሚያስጠሩ ተጫዋቾች በልጅነታቸው መኮትኮት አለባቸው ብሎ ኮካ ኮላ ያምናል፡፡ እንደሚታወቀው የኮካ ኮላ ዋና አላማ በፌድራል እና ክልል ደረጃ የእግርኳስ ተሰጥኦ ያላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ማሳተፍ እና እድል በማመቻቸት የአዳዲስ የሃገር ተስፋዋች ማፍራት ነው፡፡”

 

በውድድሩ ላይ ተስጥኦ ያላቸውን ተጫዋቾች የመልመል ስራ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከፌድሬሽኑ ጋር በመተባበር የሚሰራ ይሆናል፡፡ የአካዳሚው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ወልደገብርኤል መዝገቡ ውድድሩ የኢትዮጵያን እግርኳስ መሰረት አስይዞ በማሳደግ ላይ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ “በዚሁ ውድድር የብዙ ህፃናት ህልም እውን እንደሆነ እንደኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በልበ ሙሉነት ለመመስከር እንችላለን፡፡ አካዳሚያችን በኮፓ ኮካ ኮላ ቻምፒዮና ላይ ወጣቶች በመመልመል የበኩሉን የእድሜ ችግርን ውድድሩ ለመቅረፍ ችሎልናል እንዲሁም ተጫዋቾች ለመመልመል ችለናል፡፡ ተሳታፊ ተጫዋቾቹ ከመላው የሃገሪቱ ክፍል የሚመጡ ስለሆነ እና የአካዳሚውን የእድሜ መስፈርት የሚያሟሉ በመሆናቸው ተስፋ ሰጪ እና ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾችን ለማግኘት የቻልንበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡”

በታዳጊ ወጣቶች ስልጠና እና የኮፓ ኮካ ኮላ ውድድር አስፈላጊነት ላይ የፓናል ውይይትም ተደርጓል፡፡ የፓናል ውይይቱን የስፖርት ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ፣ የኢትዮጵያ መድን ስፖርት ክለብ የቴክኒክ ዳይሬክተር መሃመድ ኢብራሂም ፣ የወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ጣልያናዊው አሰልጣኝ አንድሪያ ሮቤሮ እና አምና በነበረው የማጠቃለያ ውድድር ኮከብ ግብ አግቢ ሆና ያጠናቀቀችው ትግስት አዲሱ በፓናል ውይይቱ ላይ ልምዳቸው አካፍለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *