የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የዛሬ ውሎ

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የዛሬ መርሃግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን ሲያሸንፍ ባህር ዳር ከተማ ከ ፋሲል ያለ ግብ ተለያይተዋል።

ባህርዳር ከተማ 0-0 ፋሲል ከነማ

ባህርዳር ከተማዎች ገና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አጥቂያቸውን ዓሊ ሱሌይማን ከሰዒድ ሀሰን ጋር ከኳስ ጋር በነበረ ፍትጊያ ዓሊ ሱሌይማን በገጠመው የትከሻ ጉዳት በኪዳነማርያም ተስፋዬ ከሜዳ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

እምብዛም ሳቢ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት ያልቻልንበት ነበር። በንፅፅር በአጋማሹ የተሻሉ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በሜዳው የላይኛው ክፍል ጫና በማሳደር እና ኳሶችን ዳግም ለማግኘት የተሻለ ጥረትን አድርገዋል።

 

በአጋማሹም ፋሲሎች ከሳጥን ውጭ ከሚመቱ ኳሶች በንፅፅር የተሻሉ የሚባሉ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። በዚህም ኦኪኪ አፎላቢ ከቅጣት ምት እንዲሁም በረከት ደስታ በሁለት አጋጣሚዎች እና ሀብታሙ ተከስተ ያደረጓቸው ሙከራዎች የባህርዳርን ግብ ለመፈተሽ ሞክረዋል። በአንፃሩ ከራሳቸው ሜዳ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ማደግ ባይችሉም ባህርዳር ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመወሰድ ጥረት አድርገዋል። በአጋማሹ በተመሳሳይ ባህር ዳር ከተማዎች በ39ኛው ደቂቃ ፍፁም ዓለሙ በቀጥታ ከቅጣት ምት ሞክሮ ሚኬል ሳማኬ በቀላሉ ከያዘበት ኳስ ውጭ ወደ ፋሲል ሳጥን ቀርበው አልተመለከትንም።

 

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተወሰነ መልኩ የመነቃቃት ምልክቶችን አሳይቶ የነበረው ጨዋታ በሒደት እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ቅዝቅዝ ያለ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በ48ኛው ደቂቃ በባህርዳሮች በኩል ዜናው ፈረደ በግሩም ሁኔታ ከተከላካዮች ጀርባ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ኪዳነማርያም ተስፋዬ ሞክሮ ሳማኪ ያዳነበት ኳስ በባህርዳር በኩል እንዲሁም በ60ኛው ደቂቃ ፍፁም አለሙ መሀል ሜዳ የተሳሳተውን ኳስ ፋሲል ከተማዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት የፈጠሩትን አጋጣሚ ኦኪኪ አፎላቢ አስቆጠረ ሲባል ሳይጠበቅ ያመከነውና በ90ኛው ደቂቃ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ያመከነው ኳስ በፋሲል በኩል ተጠቃሽ የአጋማሹ ሙከራዎች ነበሩ።

ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ በጨዋታው ባህር ዳር ከተማን በአምበልነት የመራው አህመድ ረሺድ የጨዋታው ኮከብ በመባል የዋንጫ እና የ12ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል።


ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማዎች የተሻሉ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመጨረሻው የሜዳ ሲሶ ዕድሎችን መፍጠር ባይችሉም በጥሩ የኳስ ቅብብል በተጋጣሚያቸው ላይ የበላይነት ወስደው ለመጫወት ችለዋል። በአንፃሩ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በግለሰቦች በኩል ከሚደረጉ ጥረቶች ውጭ እንደ ቡድን በመጫወት ረገድ በርካታ ክፍተቶች ያስተዋልንበት አጋማሽ ነበር። በ16ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም የተገኘ የቅጣት ምት በቀጥታ በግሩም ሁኔታ ቢመታም አዲሱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብጠባቂ ቻርለስ ሉክዋጎ በአስደናቂ ቅልጥፍና አድኖበታል።

በአጋማሹ ጥሩ ያልነበሩት ጊዮርጊሶች በ39ኛው ደቂቃ ሳጥን ውስጥ ደስታ ደሙ ሊያሻማ ሲል አሜ መሀመድ ጥፋት በመስራቱ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሀይደር ሸረፋ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹ እየመሩ ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመሩ አስችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ተሻሽለው የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሲሞክሩ አዳማ ከተማዎች ደግሞ ከመጀመሪያ አጋማሽ በተለየ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ጀርባ የሚገኙ ክፍት ሜዳዎችን ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች በአዎንታዊ የተጫዋቾች ቅያሬዎቻቸው ታግዘው ጥሩ የተንቀሳቀሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጥቃቶችን የሰነዘሩ ሲሆን በ80ኛው ደቂቃ ኢስማኤል አጎሮ ከሳጥን ፊት ለፊት የአዳማ ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ግብ የሞከረውና ግብጠባቂ የያዘበት፣ በ84ኛው ደቂቃ ከመስመር ደስታ ደሙ ያሻማውን ዳግማዊ አርዓያ ከአዳማ ተከላካዮች ሾልኮ የሞከራት እና ለጥቂት ወደ ውጭ በወጣችበት እንዲሁም በ91ኛው ደቂቃ አብርሃም ጌታቸው ከሳጥን ውጭ በቀጥታ መትቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳሶች የፈረሰኞቹን የመጨረሻ ደቂቃ ጫና ማሳያ ነበሩ።

ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የአብስራ ተስፋዬ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተመረጠ ሲሆን ከአዘጋጆቹም የዋንጫ እና የ12ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።