በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ልምምዱን በካፍ የልህቀት ማዕከል እየከወነ ይገኛል።
በኮቪድ ምክንያት ወደ 2022 ለተዘዋወረው እና በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የአህጉሩ ብሔራዊ ቡድኖች ከቀናቶች በኋላ የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ ጨዋታቸውን ማድረግ ይጀምራሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በማጣሪያው ጨዋታ ከዩጋንዳ አቻው ጋር የተደለደለ ሲሆን ዝግጅቱንም ከስድስት ቀናት በፊት ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልህቀት ማዕከል ጀምሯል።
ለዝግጅቱ ከሳምንት በፊት ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉት አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም ከመከላከያ ከተመረጠችው የግብ ዘብ አባይነሽ ኤርቄሎ ውጪ ያሉትን 33 ተጫዋቾች አግኝተዋል። አባይነሽ በግል ጉዳይ ላይ ባቀረበችው ምክንያት እስከ አሁን ስብስቡን ባለመቀላቀሏም እንደተቀነሰችም ለማወቅ ተችሏል። ከአባይነሽ ውጪ የአጥቂ መስመር ተጫዋቿ ሎዛ አበራ የቡድኑ አባላት ምርመራ ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ ቡድኑን ብትቀላቀልም እስከ ትናንት ድረስ የቀለም ትምህርት ፈተና ላይ ስለነበረች ልምምድ መስራት አልጀመረችም ነበር። በዛሬው ዕለት ግን ሙሉ ለሙሉ ከአጋሮቿ ጋር መደበኛ ልምምዷን እየሰራች እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የሀገር ውስጥ የሴቶች ውድድር ከተገባደደ ረጅም ወራቶች መቆጠራቸውን ተከትሎ ተጫዋቾቹን ለጨዋታ ዝግጁ ለማድረግ አሠልጣኝ ብርሃኑ እና ረዳቶቹ በቀን ሁለት ጊዜ ጠንከር ያለ ልምምድ እያሰሩ እንደሚገኙ ታዝበናል። በዋናነት ደግሞ የአካል ብቃት ላይ ያተኮረ ከኳስ እና ከኳስ ውጪ ያሉ ሥራዎች በልምምዶቹ ሲሰጡ ነበር። ከዩጋንዳ ጋር የሚደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ጥቅምት 10 ካምፓላ ላይ ከመደረጉ አንድ ሳምንት በፊት ደግሞ የቡድኑ የልምምድ መርሐ-ግብር በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ሆኖ የቅንጅት ስራዎች ላይ እንደሚያተኩር ተጠቁሟል።
ቡድኑ ልምምድ ከመስራቱ በተጨማሪም አቋሙን እንዲገመግም የፊታችን ቅዳሜ 3 ሰዓት በካፍ የልህቀት ማዕከል ከ2 ዓመታት በፊት በአሠልጣኝ ኤርሚያስ እየተመራ ወደ ቻይና ከተጓዘው የኢትዮጵያ ከ13 በታች ቡድን (አሁን ከ15 ዓመት በታች) ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል። ብሔራዊ ቡድኑም ጥቅምት 10 የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ ካምፓላ ላይ የሚያደርግ ሲሆን ከስድስት ቀናት በኋላ ደግሞ የመልሱን ጨዋታ ባህር ዳር ላይ የሚያከናውን ይሆናል።