“ዶሊሲ ላይ ግብ ማግባት እንፈልጋለን” ማርት ኖይ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ምድብ ለመግባት 180 ደቂቃዎች ቀርተውታል፡፡ የኮንጎ ሪፐብሊኩን ሃያል ክለብ ኤሲ ሊዮፓርድስን በአንደኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ዶሊሲ ላይ ይገጥማል፡፡

በ2013 ወደ ምድብ ለመግባት ከጫፍ ደርሶ በግብፁ ዛማሌክ ተሸንፎ የወደቁት ፈረሰኞች ማሻሻየ በተደረገበት የምድብ ድልድል ውስጥ ከሌሎቹ አመታት በተሻለ ጥሩ እድልን ይዘዋል፡፡ ሆላንዳዊው የክለቡ አሰልጣኝ ማርት ኖይ ደደቢትን በ17ኛ ሳምንት የሊግ መርሃ ግብር ከረቱ በኃላ አስጊ የሆነ የተጫዋቾች ጉዳት አለመኖሩ በተሻለ መልኩ ለቻምፒየንስ ሊግ እንዲዘጋጁ እንደረዳቸው ጠቁመዋል፡፡ “ዝግጅታችን በጥሩ መልኩ ነው የሄደው፡፡ ከደደቢት ጨዋታ በኃላ አሳሳቢ የሆነ የተጫዋቾች ጉዳት የለብንም፡፡ የረጅም ግዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው አሉላ ግርማ፣ ምንያህል ተሾመ እና ራምኬል ሎክ ብቻ ናቸው ጉዳት ላይ የሚገኙት፡፡ ከያዝናቸው 26 ተጫዋቾች 23ቱ ከጉዳት ነፃ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው 18 ተጫዋቾችን ብቻ ነው ልንይዝ የምንችለው፡፡”

ተጋጣሚያቸውን ለመመልከት መቻላቸውን የጠቆሙት ኖይ ሊዮፓርድስ ልምድ ያለው ቡድን በመሆኑ ጥንቃቄ የሚያሻው ጨዋታ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ “አዎ የተወሰኑ ምስሎችን ስለተጋጣሚያችን አይቻለው፡፡ እኔ እንደማስበው ልምድ ያለው ጠንካራ እና በተክለ ሰውነት የገዘፉ ተጫዋቾች የሚገኙበት ቡድን ነው፡፡ ቢሆን የምንመጣጠን ይመስለኛል፡፡”

በቅድመ ማጣሪያው ዙር ግብ ሳያስተናግድ የሲሸልሱን ኮት ደኦር መርታት መቻላቸው አሰልጣኙን ለቀጣዩ ጨዋታ አስፈላጊ ግብአት እንዲወስዱ ማስቻሉን ገልፀዋል፡፡ “ወሳኙ እና ትምህርት የወሰድንበት ነገር በመጀመሪያ አህጉር ጨዋታችን ግብ ሳናስተናግድ ማለፋችን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሌላ የኢትዮጵያ ክለብ ከኮት ደኦር ጋር ተጋጥሞ 2 ግቦችን አስተናግዷል፡፡ ተጋጣሚ ግብ የሚያስቆጥር ከሆነ ሁሌም ችግር ውስጥ ትገባለህ፡፡ እንደባርሰሎና እና ፒኤስጂ ጨዋታ የግቦች ፌሽታ የነበረበትን ሁኔታ እኛ ጋር እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡ ዶሊሲ ላይ ግብ ማግባት እንፈልጋለን፡፡ በተመሳሳይም ብዙ ግቦችን ማስተናገድ አንፈልግም፡፡ የጨዋታ እቅዳችን በፕሪምየር ሊጉ ላይ እንደምናደርገው ነው የሚሆነው፡፡ ብዙ ስትራቴጂዎችን የመለወጥ ሃሳብ የለኝም፡፡ ምንአልባት በተክሰ ሰውነት የገዘፉ እና ጠንካራ ተጫዋቾችን ይዘን ወደ ሜዳ ልንገባ እንችላለን እንጂ በአቀራረብ ደረጃ የተለየ ነገር አይኖርም፡፡”

አሰልጣኝ ኖይ ጨምረው አሁን ላይ ሙሉ ትኩረታቸው ከሊዮፓርድስ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ብቻ መሆኑን ጠቁመው ቡድናቸው በዘንድሮው አመት የአፍሪካ ታላቁ የክለቦች ውድድር ሩቅ ለመሄድ እንሚያልሙ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *