የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) በሳምንቱ መጨረሻ በሚደረጉት የ2017 ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች የሚመሩ ዳኞችን ይፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ዳኞች በቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የአንደኛ ዙር ጨዋታዎችን እንዲመሩ ከተመረጡ አፍሪካዊያን ዳኞች መካከል ናቸው፡፡ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የአንደኛ ዙር ጨዋታ ሶስ ላይ ዕሁድ የቱኒዚያው ቻምፒዮን ኤቷል ደ ሳህል ከኮትዲቯሩ አሶሴሽን ስፖርቲቭ ደ ታንዳ ጋር በስታደ ኦሎምፒክ ደ ሶስ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንዲመራ የፊፋ ኢንተርናሽናል የመሃል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በካፍ ተሹሟል፡፡ ባምላክ ረዳቶች የሆኑት ክንዴ ሙሴ እና ትግል ግዛው ሲሆኑ በአራተኛ ዳኛነት ዘካሪያስ ግርማ ተመርጧል፡፡ ረዳት ዳኞች ትግል እና ክንዴ ከዚህ ቀደም በቅድመ ማጣሪያ የቻምፒየንስ ሊግ ናይሮቢ ላይ የተስካር እና ኤኤስ ፖር ሉዊ 2000 ጨዋታን መምራታቸው ይታወሳል፡፡
የዲ.ሪ. ኮንጎው ሳንጋ ባላንዴ ሉቡምባሺ ላይ የሱዳኑን አል ሂላል ኦባያድን የሚያስተናግድበትን የስታደ ኪባሳ ማሊባ ጨዋታ እንዲመራ ሃይለየሱስ ባዘዘው ተመርጧል፡፡ የ2007 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ዳኛ ሃይለየሱስ ባዘዘው በተመሳሳይ ውድድር በቅድመ ማጣሪያውን ኪጋሊ ላይ የሩዋንዳውን ራዮን ስፖርት እና የደቡብ ሱዳኑን አል ሰላም ጨዋታን መምራቱ ይታወሳል፡፡ የሃይለየሱስ ረዳቶች ሆነው የተመረጡት ተመስገን ሳሙኤል እና ክንፈ ይልማ ናቸው፡፡ በአራተኛ ዳኛነት የ2008 የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ዳኛ በላይ ታደሰ ሆኗል፡፡
በተያያዘ ዶሊሲ ላይ በሚደረገው ኤሲ ሊዮፓርድስ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታን እንዲመሩ ኮትዲቯራዊያን ዳኞች ተሹመዋል፡፡ የመሃል ዳኛ ጃን ጃክዌስ ንጋምቦ እና ረዳቶቻቸው ኦሊቨር ካቤኔ እና ባባካ ማምፓሲ ጨዋታን ይመራሉ፡፡ አዲስ አበባ ላይ የሚደረገው የመልስ ጨዋታ ሶማሊያዊያን ዳኞች የሆኑት ሃሰን መሃመድ ሃጊ እና ረዳቶቻቸው አህመድ ፋራህ እና አብዱላሂ አዊስ ሆነዋል፡፡