“ፍላጎታችን ወጣት ተጫዋቾችን በማብቃት ወደ ውጪ ሃገራት ማዘዋወር ነው” ዴቪድ በሻ እና ስቲቭን ሄኒንግ

የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካይ ዴቪድ በሻ ከጀርመናዊው ወኪል ስቲቨን ሄኒንግ ጋር በጋራ በታዳጊ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ላይ ለመስራት ከስምምነት መድረሱን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡

በስምምቱ መሰረት ወጣት ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ወደ አውሮፓ ሃገራት ሄደው የሚጫወቱበትን እድል መክፍት ዋነኛው አላማው አድርጎ መነሳቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጀርመን፣ ቡልጋሪያ፣ ታይላንድ እና ሆንግ ኮንጎ እግርኳስን የተጫወተው የአሁኑ የተጫዋቾች ወኪል ሄኒንግ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ከሆነ ተጫዋቾቹን ከዝውውሮቹ አስቀድሞ የማብቃት ስራ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡ “አሁን ላይ ወጣት የኢትዮጵያ ተጫዋቾችን ወደ አውሮፓ ለማምጣት እኔ እና ዴቪድ የጋራ ስምምነትን አድርገናል፡፡ ይህ ዋነኛ ግባችን ነው፡፡ በተለይ ወደ አውሮፓ ከማቅናታቸው በፊት ተጫዋቾቹን በአእምሮ ረገድ ለማዘጋጀት፣ ሊወስዷቸው ስለሚገቡ ለውጦች ለማስረዳት፣ የታክቲክ ትምህርቶች እና ቋንቋን ለማስተማር አቅደናል፡፡ ቋንቋ መማራቸው እና ሌሎቹን ነገሮች ማወቃቸው ወደ አውሮፓ ሲያቀኑ በቶሎ ከቦታው እና ባህሉ ጋር መዋሃድ ይችላሉ፡፡ በአውሮፓ ጠንካራ ሊጎች ውስጥ የሚጫወቱ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾችን ወደፊት እንደምናይ ተስፋ አደርጋለው፡፡ ፈታኝ እና ረጅም ሂደት ነው የሚሆነው ግን በስራው ከፍተኛ እምነት አለን፡፡”

ዴቪድ በበኩሉ ሄኒንግ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳያቱ ወደ ስራው እንዲገቡ እንዳስቻላቸው አስረድቷል፡፡ “ ስቲቨንን ማግኘት ከጀመርኩ ከዓመት በላይ ይሆነኛል፡፡ ስራ ስጀምር በቀላሉ ከበርካታ ወኪሎች ጋር አገኝ ነበር፡፡ ፍላጎት አስይቶ መምጣት የቻለው ግን እሱ ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ እምነቱን ጥሎ ወደ አፍሪካ ለስራ የሚመጣ አንድም ጀርመናዊ ወኪል አይገኝም፡፡ ለዚህም እሱን ማመስገን እፈልጋለው፡፡ እራሱን በስራ ያሳየ አጋርን ለማግኘት በድርጄቴ በኩል ፍላጎት ስለነበር የስቲቨን መምጣት አዎንታዊ ጎን አለው፡፡ ፍላጎታችን ወጣት ተጫዋቾችን በሚገባ እና በበለጠ መንገድ አዘጋጅቶ ወደ ውጪ ሃገር ለመውሰድ ነው፡፡”

ድርጅቱ እስካሁን የሶስት ተጫዋቾች ወኪል ለመሆን ሲስማማ በቀጣዮቹ ሳምንታት ቁጥሩ እንደሚያድግ ተነግሯል፡፡ የደደቢቱ እያሱ ተስፋዬ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በውሰት ለአራዳ ክፍለ ከተማ የሚጫወተው ሚኪያስ ግርማ እና ለኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን መጫወት የቻለው ሉክ ፖል በድርጅቱ ለመወከል ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ የተቀሩት ሌሎች ተጫዋቾችን ስም ግን ጉዳዮቹ ባለመጠናቀቃቸው ለመግለፅ እንደማይችሉ ሄኒንግ ተናግሯል፡፡ ድርጅቱ ተጫዋቾች ውል ሲያስፈርም ህጉን የተከተለ መሆኑን ተነግሯል፡፡ ከወጣት ተጫዋቾች ጋር ለመስራትም ከቤተሶባቻቸው ጋር ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ወላጆች እና አሳዳጊዎች የውል ስምምነቶችን እንዲረዱም በማድረግ ላይ እንዳለ ዴቪድ በአስተያየቱ ጠቅሷል፡፡

ለተጫዋቾቹ የአውሮፓ እድልን ከመፍጠር ባሻገር ብቁ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን መልማዮች የሚመሩ የታዳጊ ፕሮጀክቶችን በሃገሪቱ ሌሎች ስፍራዎች መክፈት እንደእቅድ ተጠቀምጧል፡፡ በተለይ በጋምቤላ ክልል የታዳጊ ፕሮጀክቶችን የመክፈት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ድርጅቱ ገልጿል፡፡ ብቁ ነን ብለው የሚያስቡ የታዳጊ እግርኳስ ላይ የሚሰሩ አሰልጣኞች ጋር ለመስራት ፍላጎት ያለው እንደሆነ ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ ከወጣት ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ባሻገር ጥሩ የብቃት ደረጃ ያላቸውን አፍሪካዊያን እና ትውልደ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከታቀዱት ስራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ እንደሄኒንግ ገለፃ ከሆነ በፕሪምየር ሊጉ አሁን ላይ የሚጫወቱት አብዛኞቹ የአፍሪካ ተጫዋቾች የብቃት ደረጃቸው በጣም የወረደ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የዴቪድ እግርኳስ አማካሪን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ዴቪድ የኢትዮጵያ ቡና እና የብሄራዊ ቡድን አማካይ የሆነው የጋቶች ፓኖም ወኪል በመሆን ያገለግላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *