የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየተሳተፈበት በሚገኘው የካፍ 2017 ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ምድብ ለመግባት ከኮንጎ ሪፐብሊኩ ክለብ ኤሲ ሊዮፓርድስ ጋር ዶሊሲ ላይ ይጫወታል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣሪያው የሲሸልሱን ኮት ደኦር 5-0 በመርታት ወደ አንደኛው ዙር ሲያልፍ ሊዮፓርድስ በበኩሉ የካሜሮኑን ዩኤምኤስ ደ ሉምን ከሜዳው ውጪ ባስቆጠረው ግብ ታግዞ መርታት ችሏል፡፡ ከጉዳት መልስ ከፈረሰኞቹ ጥንካሬን እያላበሱ የሚገኙት የመሃል ተከላካዮ ሰልሃዲን ባርጌቾ እና የመስመር አማካዩ በኃይሉ አሰፋ እሁድ ስላለባቸው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
“ጥሩ ውጤት አምጥተን ለቀጣዩ ዙር መነሳሻ ይሆነናል” ሰልሃዲን ባርጌቾ
“ቡድናችን በጥሩ ሁኔታ ላይ በመገኘቱ ጥሩ ዝግጅት እንዳናደርግ አግዞናል፡፡ ከአላህ ጋር ጥሩ ውጤት እናመጣለን ብዬ አስባለው፡፡”
“እንደሚታወቀው ከአንድ ዓመት በኃላ ነው ወደ ሜዳ መመለስ የቻልኩት፡፡ ከተመለስኩ በኃላ ጥሩ አቋም ላይ ነው ያለሁት፡፡ አሁን ላይ በጥሩ ጤንነት ላይ እገኛለው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ቡድኑም ከሶስት ተጫዋቾች በስተቀር በጥሩ ጤንነት ላይ ስለምንገኘ ጥሩ ውጤት እናመጣለን ብዬ አስባለው፡፡”
“እንደእቅድ የመጀመሪያው ጨዋታ ከሜዳ ውጪ መሆኑ በጣም ጥሩ ነው ለእኛ፡፡ ስለተጋጣሚያችን ብዙም ነገር አናውቅም እና እንደዚህ ነው እንደዚህ ነው ብለን አንሄድም፡፡ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃ ጨዋታውን ለማንበብ እንሞክራለን ከዛ በኃላ አሰልጣኞቻችን የሚሰጡን መመሪያ ተክትለን የራሳችንን ስራ እንሰራለን ብዬ ነው ማምነው፡፡ ጥሩ ውጤት አምጥተን ለቀጣዩ ዙር መነሳሻ ይሆነናል ብዬ አስባለው፡፡”
“ብዙ ፈተናዎች ከሜዳ ውጪ ሊኖሩ ይችላሉ” በኃይሉ አሰፋ
“የመጀመሪያውን ዙር አልፈን አሁን ላይ ደግሞ ለሁለተኛው ዙር የሚረዳንን ዝግጅት አድርገናል፡፡ እግርኳስ ባለፈው ታሪክ የምትጫወተው አይደለም፡፡ በብዙ ሁኔታዎች በአለም እግርኳስ ብዙ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡ ለምሳሌ 4-0 ተሸንፎ የነበረ ቡድን ዛሬ 6-1 አሸንፎ ሲያልፍ ተመልክተናል፡፡ ይህ ለእኛ ትምህርት ነው ሁሉንም ነገር ማድረግ እንድምንችል፡፡ ነገር ግን እግርኳስ ባለፈ ነገር ሳይሆን በወቅታዊ አቋም ወይም በእለቱ በምታሳየው እንቅስቃሴ ነው ውጤቱ የሚወሰነው፡፡ ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ማድረጋችን ለጨዋታው ብቁ ሆነን እንድንቀርብ ያስችለናል፡፡”
“በትንሽም ቢሆን ሊዮፓርድስ ከካሜሮን ዩኤምኤስ ደ ሎም ጋር ያደረገውን ጨዋታ ለማየት ችለናል፡፡ ምስሎችን ለማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም ብዙም ባይሆን የተወሰነ ነገር ስለቡድኑ ማወቅ ችለናል፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብን እና ስለምንከተለው የጨዋታ ስልት ላይ በተንቀሳቃሽ ምስል መመልከት ችለናል፡፡”
“የመጀመሪያ ጨዋታችን ከሜዳ ውጪ ነው ከሜዳ ውጪ ያለብንን ጨዋታ ምን ማድረግ አለብን ነው የመጀመሪያው ስራችን፡፡ በመጀመሪያ የቤት ስራችንን እዛው ጨረሰን ለመምጣት ነው የምንፈልገው፡፡ ምናገኛቸውን እድሎች መጠቀም የምንችል ከሆነ ወደ ምድብ ለመግባት የሚያስችለንን ውጤት ይዘን እንመጣለን ብዬ አስባለው፡፡ ብዙ ፈተናዎች ከሜዳ ውጪ ሊኖሩ ይችላሉ ቢሆንም የመልስ ጨዋታው ቀላል ለማድረግ የቤት ስራችንን እዛው መጨረስ አለብን፡፡ የምንችለውን ነገር በእኛ በኩል ለማድረግ ዝግጁ ነን፡፡”