በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የእለተ ቅዳሜ ብቸኛ መርሀ ግብር አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ወልዲያን ያስተናገደው ደደቢት በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 31 አሳድጎ ነገ ጨዋታውን የሚያደርገው ሲዳማ ቡናን በግብ ልዩነት በመብለጥ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡
ደደቢቶች ባሳለፍነው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈው ቡድናቸው የ6 ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ እና ወደ ቀድሞው የ4-4-2 አሰላለፍ በመመለስ ነበር ጨዋታውን መጀመር የቻሉት፡፡ ታሪክ ጌትነት በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመርያ 11 ውስጥ መግባት ሲችል ፤ ተከላካይ ስፍራ ላይ በጉዳት እና በቅጣት የሌሉት ስዩም ተስፋዬ እና ብርሃኑ ቦጋለን በመተካት ደስታ ደሙ እና ሰለሞን ሀብቴ በቀኝ እና በግራ ተከላካይነት ተሰልፈዋል፡፡ በቅዳሜው ጨዋታ በ5 ቢጫ ምክንያት ያልተሰለፈው ከድር ኩሊባሊ ዳግም ወደ ቡድኑ ሲመለስ በግራ መስመር ላይ ኤፍሬም አሻሞ ወደቀደመ ቦታው በቋሚነት ተመልሷል፡፡ በአንፃሩ ወልዲያዎች ባሳለለፍነው ሳምንት ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 1-1 ከተለያየው ቡድን ለውጥ ሳያደርጉ በተመሳሳይ ተጫዋቾች ወደ ጨዋታው ገብተዋል፡፡
ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል እምብዛም ግልጽ የግብ ማስቆጠር እድሎች አልታዩበትም፡፡ በ5ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከቋመ ኳስ ሞክሮ ኤሚክሬል ቤሌንጌ እና የግቡ ቋሚ ተጋግዘው የመለሱት ኳስ በመጀመሪያ አጋማሽ ከታዩት ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበረች፡፡ በዚሁ የመጀመሪያ አጋማሽ ወልዲያዎች በተለይም በቀኝ መስመር በኩል በያሬድ ሀሰን አማካኝነት በተደጋጋሚ ወደ ደደቢቶች የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ ነገርግን ይህ ነው የሚባል የግብ ማግባት እድሎችን መፍጠር አልቻሉም፡፡
በጨዋታው ደደቢትን በአምበልነት እየመራ ወደ ጨዋታው የገባው አጥቂው ዳዊት ፍቃዱ በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኛቸውን ሁለት ግልፅ የሆኑ የማግባት አጋጣሚዎችን ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡
ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከ5 ደቂቃዎች በኃላ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኘችውን ኳስ ዳዊት ፍቃዱ አመቻችቶ ያቀበለውን ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ በግሩም ሆኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ይህችም ግብ ጌታነህ ከበደ በሊጉ ያስቆጠራት 13ኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ በነበሩት ሁለት ደቂቃዎችም ደደቢቶች በሰለሞን ሀብቴ ፣ ዳዊት ፍቃዱ እና ጌታነህ ከበደ በተከታታይ ያገኟቸውን የግብ ማግባት እድሎች ሳይጠቀምባቸው ቀርተዋል፡፡
ወልድያዎች ከግቡ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን በ55ኛው ደቂቃ ከደደቢት በውሰት ውል በውድድሩ ዘመኑ አጋማሽ ወልዲያን የተቀላቀለው ያሬድ ብርሃኑ ቡድኑ አቻ ሊሆን የሚችለበትን ወርቃማ አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
በ73ኛው ደቂቃ ላይ ደደቢቶች መሪነታቸውን ማስፋት የሚችሉበትን አጋጣሚ የወልዲያው የመሀል ተከላካይ ያሬድ ዘውድነህ የሰውነት ሚዛኑን መጠበቀ ሳይችል ቀርቶ በመውደቁ ምክንያት አግኝተው ኤፍሬም አሻሞ ከወልዲያ ግብ ጠባቂ ቤሌንጌ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
በጨዋታው መገባደጃ ላይ ወልዲያ ከመስመር ያሻማሙትን ኳስ ቁመተ መለሎው አጥቂ በድሩ ኑርሁሴን በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ለትማ ተመልሳለች፡፡ የተመለሰችውን ኳስ አንዱአለም ንጉሴ በድጋሚ ቢሞክርም ካድር ኩሊባሊ ከመስመር ላይ በማውጣት ግብ ከመሆን አድኗት ጨዋታው በደደቢት 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በዚህ ውጤት መሠረት ደደቢት ከ18 ጨዋታዎች 31 ነጥብ በመሠብሰብ በነገው እለት ሌሎች ቡድኖች ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ ድረስ በ2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወልድያ አሁንም በ8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡