ኤልያስ ኢብራሂም – የደደቢት ምክትል አሰልጣኝ
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታው በሁለተኛው ዙር መጀመሪያ ካደረግናቸው ሁለት ጨዋታዎች የተሻለ እንቅስቃሴ እና የተሻለ ውጤት ያገኘንበት ጨዋታ ነበር፡፡”
በጉዳት ቡድናቸው ስለመሳሳቱ
“ትኩረት አድርገን እየሰራን የምንገኘው ወጣቶች ላይ ነው፡፡ ምንም እንኳን በርካታ ተጫዋቾችን በጉዳት ብናጣም ብቁ የሆኑ ወጣት ተጫዋቾች ስላሉን የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በወጣቶቹ ለመሸፈን እየሞከረን እንገኛለን፡፡”
ስለ ጨዋታው ውጤት
“በጨዋታው ከነበረው እንቅስቃሴ አንጻር የተወሰኑ ኳሶችን ወደ ግብነት መቀየር ነበረብን፡፡ ነገርግን አጠቃላይ ከነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ አንጻር ውጤቱ የሚገባን ነበር፡፡”
አቤል እንዳለ በጨዋታው ካሳየው ድንቅ አቋም የተነሳ የአስራት መገርሳ ከጉዳት ሲመለስ ከቋሚ አሰላለፍ ስለማስወጣት
“እንደሚታወቀው የቋሚ ተሰላፊነት እድል በወቅታዊ አቋም የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ በልምምድ ላይ በሚያሳዩት አቋም የሚወስን ይሆናል፡፡”
ንጉሴ ደስታ- የወልዲያ አሰልጣኝ
ስለ ጨዋታው
“የዛሬው ጨዋታ ላይ በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ነበርን፤ እናሸንፋለን ብለን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው ነገርግን ተጋጣሚያችን በልምድ እና በብልጠታቸው በመጠቀም ባስቆጠሯት አንድ ግብ አሸንፈውናል፡፡”
በተደጋጋሚ አቻ መውጣታቸው በሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ጥረት ላይ ያለው ችግር
“እንግዲህ ላለመውረድ ብለን የምናልመው ነገር የለም ፤ ያሉብንን ችግሮች እያቃለልን ባቀድነው እቅድ መሠረት እየሄድን እንገኛለን፡፡ በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎቻችን ላይ አቻ እየወጣን ነበር ነጥቦችን የሰበሰብነው፡፡ ነገርግን አሁን በተለይም በሜዳችን ላይ በምናደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የአሸናፊነት ስሜትን ነበር ይዘን የምንገባው ነገርግን በቀላሉ ግቦችን እያስተናገድን ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን ችግር ቀርፈን ጨዋታዎችን በማሸነፍ የበለጠ በሊጉ የምንቆይበትን እድሎች ለመፍጠር የበለጠ ጥረት እናደርጋለን፡፡”
ስለተጋጣሚያቸው
“በእኔ እይታ ደደቢት የተሟላ ቡድን ነው ፤ እከሌ ስለወጣ እከሌ ስለገባ የምትለው ቡድን አይደለም፡፡ በዛሬው ጨዋታ ላይ ሶስት ተጠባባቂ ተጫዋቾችን ይዘው ቢገቡም ጥሩ አቅም ያላቸው ተፎካካሪ ልጆች በመሆናቸው በብልጠት አሸንፈውናል፡፡”