ኢትዮጵያ ቡና ከሜዳው ውጭ ወርቃማ ሦስት ነጥቦችን አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጎንደር አጼ ፋሲለደስ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ 4-1 ተሸንፏል፡፡ ማራኪ ፍሰት የታየበት ፣ አስገራሚ እና ኋላ ላይ ወደ ነውጥ ያመራ የደጋፊ ድባብ ፣ በግሩም ጎሎች የታጀበ ጨዋታ  የጎንደር አፄ ፋሲል ስቴዲዮም የዛሬ ትዕይት ነበር ።

በሁለቱ ቡድኖች የደጋፊ ማህበር በመልካም ግንኙነትና የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊ ማህበር ለፋሲል ከተማ ደጋፊዎች የስጦታ በመስጠት የተጀመረው ጨዋታ በነበሩት የመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ባለ ሜዳዎቹ ፋሲሎች ብልጫ በመውሰድ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ተጫውተዋል፡፡ በተለይ በኤደም ሆሮሶውቪ እና በኤርምያስ ኃይሉ አማካኝነት ለጎል የቀረበ ሙከራ ፋሲል ከተማን ቀዳሚ ማድረግ በቻሉ ነበር። 15ኛው ደቂቃ በኋላ ጨዋታው በሚገርም አጨዋወት በሁለቱም ቡድኖች በሚፈጠር ጎል አጋጣሚ ተመልካቹን ቁጭ ብድግ የሚያሰኝ ነበር።

አፄዎቹ በአንድ ደቂቃ ልዩነት ውስጥ ያገኙትን የግብ አጋጣሚ  አብዱራህማን ሙባረክ እና ኤርምያስ ኃይሉ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በአንፃሩ እንግዶቹ ቡናዎች አስቻለው ግርማ የግብ አግዳሚ የመለሰበት እና ኤልያስ ማሞ የፈጠሩት አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነበር። ሆኖም 36ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም መሀመድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ በግንባሩ አመቻችቶለት ኤልያስ ማሞ አየር ላይ በቮሊ መትቶ ግሩም ጎል በማስቆጠር ቡናዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ አፄዎቹ ተጭነው ቢጫወቱም ጎል ሳያስቆጥሩ የመጀመርያው አጋማሽ በኢትዮዽያ ቡና 1-0 በሆነ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል ለእረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ የጨዋታው መልክ በጥሩ ሁኔታ በቀጠለበት እስከ 61ኛው ደቂቃ ድረስ ፋሲሎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት በሚያደርግበት አጋጣሚ 50ኛው ደቂቃ ኤልያስ ማሞ በሚገርም ሁኔታ በሁለት ተከላካዮች መሀል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ብቻውን ከዮሐንስ ሹኩር ጋር ተገናኝቶ  ሳሙኤል ሳኑሚ ለቡና ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ የቡናን መሪነት ከፍ አድርጓል፡፡ ከጎሉ መቆጠር ብዙም ሳይቆይ ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃ ተቋርጦ ሲጀምር በተመሳሳይ ሁኔታ 61ኛው ደቂቃ ላይ  በቀኝ መስመር በአንድ ሁለት ቅብብል የገቡት ቡናዎች ሳሙኤል ሳኑሚ በሚገርም እይታ ብቻውን ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው አስቻለው ግርማ አቀብሎት አስቻለው ሦስተኛ ጎል በማስቆጠር የኢትዮዽያ ቡናን መሪነት አስፍቷል፡፡
ከጎሉ መቆጠር በኋላ አስቀድመን ከተመለከትነው አስገራሚ ድባብ በተቃራኒው በካታንጋ በኩል በተፈጠረ የድንጋይ ውርወራ ጨዋታው ለ36 ደቂቃ ተቀቋርጦ ተጀምሯል፡፡ ምርጥ እንቅስቃሴ ሲታየይበት የነበረው ጨዋታ ከተቋረጠበት ሲጀምር ብዙም ሳቢ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ 66ኛው ደቂቃ ላይ የተሰጠውን ፍ/ቅ/ም ኤዶም ሆሮሶቪ አስዎጥሮ የጎል ልየዩነቱን ማጥበብ ችሏል። በቀሩት ደቂቃ ብዙም ተጠቃሽ ሙከራ ባይኖርም የጨዋታው መጠናቀቂያ በ89ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፓኖም አስቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮዽያ ቡና የበላይነት 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በመሀል በተከሰተ ግርግር የተቋረጠው ጨዋታ በመጨረሻም በሰላም የተጠናቀቀ ሲሆን ከ700 ኪሎ ሜትሮች በላይ አቋርጠው የመጡት የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች በደስታ ከስታድዮሙ ወጥተዋል፡፡

Leave a Reply