የጨዋታ ሪፓርት | ንግድ ባንክ ከወራጅ ቀጠና ሊወጣበት የሚችልበትን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት መርሃግብር ጅማ አባቡናን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታውን ያለ ግብ በአቻ ውጤተት ፈፅሟል፡፡

ቀዝቃዛ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በመሃል ሜዳ ላይ ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ የሚቆራረጡና የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾቹ በርቀት ተነጥለው ሲባክኑ የተስተዋሉበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽም ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ አልታየም ፤ ነገርግን ጅማ አባቡናዎች ከረጅም ርቀት ያገኙትን የቅጣት ምት ተከላካዮ ልደቱ ጌታቸው ሞክሮ የግቡ አግዳሚ ከመለሳት ኳስ በስተቀር በጨዋታው እጅግ በርካታ የሆኑ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ኳሶች በሁለቱ ቡድኖች በኩል ተስተውለዋል፡፡

 

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባቡናዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ በኩል ተሽለው መቅረብ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ በተለይም በ60ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ወርቃም የግብ ማግባት አጋጣሚ አጥቂው መሀመድ ናስር ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

 

በጨዋታው ሌላው የተስተዋለው ነገር በተለምዶ ከማን አንሼ እየተባለ በሚጠራው ቦታ ላይ በርከት ያሉ የጅማ አባቡና ደጋፊዎች ሙሉ ዘጠናውን ደቂቃ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ታይተዋል፡፡

 

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ በውድድሩ አጋማሽ ላይ ካልተሳካው የድሬዳዋ ከተማ ቆይታ በኃላ በውሰት ውል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የተቀላቀለው ሮቤል ግርማ ሱራፌል አወልን በግንባሩ በመግጨቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል፡፡

 

እምብዛም ማራኪ ያልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሳይሸናነፉ 0-0 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

 

ገብረመድህን ሀይሌ – ጅማ አባቡና

 

ስለ ጨዋታው ውጤት

“በጨዋታው ውጤት ሁለት አይነት ስሜት ነው የተሰማኝ ፤ በተወሰነ መልኩ አያስከፋም ግን ደግሞ ጨዋታውን ጨርሰን ልንወጣባቸው የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

ወደ ጨዋታው ስንመጣ ለማሸነፍ ነበረ ፤ ተጋጣሚያችንም ጠንካራ ስብስብ ያለው ጠንካራ ቡድን ነው እንደአጠቃላይ ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው ቡድኖች እንደመገናኘታቸው ሳንሸነፍ  አንድ ነጥብ ይዘን መውጣታችን ጥሩ የሚባል ነው፡፡”

 

ቡድኑ ላይ በጨዋታው ስላየው ዋንኛ ክፍተት

“በተለይ በዛሬው ጨዋታ ከሌላው ጊዜ በተለየ የመሀል ሜዳችን ተሰብሮ ነበር ከአጥቂዎቻችን ጋር በፍፁም መገናኘት አልቻሉም፡፡”

 

ስለ ወራጅነት ስጋት

“በእኛ ደረጃ ለሚገኝ ቡድን እያንዳንዱ ጨዋታ ወሳኝነት አለው ፤ በተለይም በዛሬው ጨዋታ በቅርብ ርቀት አንተን የሚከተል ቡድን እንዳያሸንፍ ማድረጉ በራሱ ጥሩ ነገር ነው፡፡እንደ እቅድ አርገን የያዝነው በመጀመሪያ 4 ጨዋታዎች ነጥብ መያዝ ነበር እስካሁን በሶስቱ ጨዋታዎች አሳክተናል፡፡በቀጣይ በሚኖሩ የሜዳችን ጨዋታዎች ነጥቦችን በመያዝ ከወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ ነው እቅዳችን፡፡”

 

ሲሳይ ከበደ – ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ

ስለ ወራጅነት ስጋት

” እንደሚታወቀው ሊጉ እድሎችን ይሰጥሃል፡፡ቀጣይ ጨዋታዎች ጠንክረን ሰርተን በግልፅ የሚታዮብንን ችግሮች መቅረፍ ከቻልን አሁን ላይ ስለ መውረድ የሚወራበት ጊዜ አይደለም ፤ ቀሪ 12 ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ከቻልን አሁንም ጊዜው ገና ነው፡፡”

 

ስለ ተከላካይ ክፍሉ

“የተከላካይ ክፍሉ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ በአዳዲስ ልጆች  የተገነባ ነው፡፡ ይሄ ጥምረት ደግም ድግግሞሽ ይፈልጋል ሆኖም ግን ዛሬም አንዳንድ ስህተቶች ቢኖሩም አሁንም ግብ ሳናስተናግድ ወጥተናል በጊዜ ሂደት ይሄ ጥምረት እየተሻሻለ የሚመጣ ነው፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *