የጨዋታ ሪፓርት | አዲስ አበባ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃግብር የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ ተፈጽሟል፡፡

ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ እንደመጀመሪያው ጨዋታ ሁሉ ይህ ነው የሚባል ሳቢ የሆነ እንቅስቃሴ ሳይታይበት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በአመዛኙ በመሀል ሜዳ ላይ በተደገደቡ አጫጭር የኳስ ቅብብሎች እንዲሁም አልፎ አልፎ በቀጥተኛ አጨዋወት ከመስመር እንዲሁም ከተከላካዬች በቀጥታ በሚጣሉ ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ ቢጥሩም ሁለቱም ቡድኖች ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ የመጀመሪያው 45 ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

 

ከመጀመሪያው በመጠኑም ቢሆን የተሻለ በሚመስለው ሁለተኛው አጋማሽ 66ኛው ደቂቃ ላይ አዲስአበባ ከተማን በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የተቀላቀለው አጥቂው ጀምስ ኩዋሜ ከኤሌክትሪክ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ ያገኘውን ኳስ እንደነጠረ አግኝቶ አክርሮ በመምታት ምክሮ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡ ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር አዲስአበባ ከተማዎች ጨዋታውን ለማሸነፍ ከመሞከር ይልቅ ጊዜ በመግደል ተግባር ላይ በተለይም ግብጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ተጠምዶ ተስተውሏል፡፡

 

የጨዋታውን ውጤተት ተከትሎ አዲስአበባ ከተማ አሁንም በ10 ነጥብ በሊጉ ግርጌ ላይ ሲገኝ በአንጻሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ20 ነጥብ በ11 ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

አስራት አባተ – አዲስአበባ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ነበር፡፡ኤሌክትሪክ በሊጉ ከሚገኙ ጠንካራ ቡድኖች አንዱ ነው ፤ ከእረፍት በፊት በከፍተኛ ሆኒታ አጥቅተውን ተጫውተዋል ፤ ከእረፍት መልስ ደግሞ እኛ በተሻለ አጥቅተን የግብ እድሎችን መፍጠር ብንችልም ሳንጠቀምባቸው ቀርተናል፡፡”

 

በተከታታይ ነጥብ መጣላቸው በሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ጥረት ላይ ስለሚያሳድረው ተፅዕኖ

“ለእኛም ሆነ ለሌሎች ቡድኖች ቢሆን ጨዋታዎችን ማሸነፍ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ይህም ስለሆነ የተሻለ ተንቀሳቅሰን ጨዋታውን ለማሸነፍ ጥረት አድርገናል ነገርግን የእግርኳስ ውጤት የሚለካው በተጫወትከው እና ባስቆጠርከው ግብ ስለሆነ የሚወሰነው ይህንን ማሳካት አልቻልንም ነገርግን በቀጣይ የቀሩ ጨዋታዎችን በማሸነፍ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመገኘት እንጥራለን፡፡”

 

*የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዮ አስተያየታቸውን ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *