በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የአንደኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታዎች እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቅቀዋል፡፡ የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ድል ሲያሰመዘግብ ዛማሌክ፣ ሪቨርስ ዩናይትድ፣ አል ሂላል፣ አል አሃሊ ትሪፖሊ፣ ኤቷል ደ ሳህል፣ ኮተን ስፖርት እና ክለብ ፌሬቫያሮ ደ ቤይራ በሜዳቸው ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ዶሊሲ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደው የኮንጎ ሪፐብሊኩ ኤሲ ሊዮፓርድስ በሜዳው እና ደጋፊው ፊት 1-0 ተሸንፏል፡፡ በሜዳቸው ለማሸነፍ ከሚከብዱ የአፍሪካ ክለቦች መካከል የሚመደበው ሊዮፓርድስ ለፈረሰኞቹ እጁን ሰጥቷል፡፡ ምንተስኖት አዳና በ25ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ የቡድኖቹ ልዩነት ነበረች፡፡ ግብ አስቆጣሪው ምንተስኖት በሁለተኛው አጋማሽ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ ከ10 ደቂቃች በላይ ፈረሰኞቹ በ10 ተጫዋቾች ለመጫወት ተገደዋል፡፡ የቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመግባት ጥረት ሲያደርግ ለነበረው ክለቡ እና ደጋፊዎቹ ውጤቱ አስደሳች ሆኗል፡፡ በመጀመሪያው ዙርም ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ነው፡፡
የ2016 ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ ዛማሌክ በካይሮ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የናይጄሪያውን ኢንጉ ሬንጀርስ አስተናግዶ 4-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ የዛማሌክን የድል ግቦች ናይጄሪያዊው ስታንሊ ኦዋዉቺ፣ ሆሳም ፓውሎ፣ ሙስጠፋ ፋቲ በፍፁም ቅጣት ምት እና አይመን ኸፍኒ ከመረብ አዋህደዋል፡፡ ለኢንጉ ሬንጀርስ ባቢ ክሌመንት በሁለተኛው አጋማሽ አስቆጥሯል፡፡
የሪቨርስ ዩናይትድ ኤል ሜሪክ ላይ ሶስት ግቦች በማስቆጠር ያልተጠበቀ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ኮትዲቯራዊው አጥቂ ጋይ ኩዩሜን ሁለት ግቦች ሲያስመዘግብ ኢሶሳ ኢግቢኖባ ማሳረጊያዋን በ82ኛው ደቂቃ አስገኝቷል፡፡ የሜሪክ የከተማ ተቀናቃኙ አል ሂላል በአንፃሩ ፖር ሉዊ 2000ን በተቃራኒ 3-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሱዳናዊው አጥቂ ቢሻ ሁለት ግቦች ከመረብ ሲዋህድ ጋናዊው ኦገስቲን ኦክራ ቀሪዋን ግብ አስገኝቷል፡፡
ኢትዮጵያዊው ዳኛ ባምላክ ተሰማ ረዳቶቹ ክንዴ ሙሴ፣ ትግል ግዛው እና ዘካሪያስ ግርማ ሳስ ላይ በመሩት ጨዋታ ኤቷል ደ ሳህል ኤኤስ ታንዳን 3-0 መርታት ችሏል፡፡ የድል ግቦቹን ቦጋታስ፣ ጀማል እና ቦአዛ አስገኝተዋል፡፡
ሉቡምባሺ ላይ የ2016 ኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊው ቲፒ ማዜምቤ ከካፕስ ዩናይትድ ጋር ባልተጠበቀ መልኩ አቻ ተለያይቷል፡፡ እንግዶቹ በጨዋታው በተጀመረ ሰከንዶች ውስት በአባስ አሚዱ አማካኝነት ቀዳሚ ሲሆን ሬንፎርድ ካላባ የማዜምቤን የአቻነት ግብ ከ12 ደቂቃዎች በኃላ አስገኝቷል፡፡ ማዜምቤዎች በጨዋታው ብልጫ ወስደው ቢጫወቱም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ አስደንጋጭ ውጤትን በሜዳቸው አስመዝግበዋል፡፡
ኤኤስ ቪታ ክለብ ከሜዳው ውጪ ወደ ጋምቢያ በማቅናት ከጋምቢያ ፖርትስ ኦቶሪቲ ጋር አቻ ተለያይቷል፡፡ አላጂ ሳር የጋምቢያውን ክለብ ሲያስገኝ ፍራንሶአ ኦባማ ኦንዶ ለኪንሻሳው ሃያል ግብ አስገኝቷል፡፡
የመልስ ጨዋታዎች በያዝነው ሳምንት ከአርብ ጀምሮ መደረግ ይጀምራሉ፡፡
ዓርብ ውጤት
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ) 2-1 ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ (ዩጋንዳ)
ቅዳሜ ውጤቶች
ያንግ አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) 1-1 ዛናኮ (ዛምቢያ)
ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ) 3-1 ሆሮያ (ጊኒ)
አል አሃሊ (ግብፅ) 1-0 ቤድቬስት ዊትስ (ደቡብ አፍሪካ)
ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ) 1-0 ሞናና (ጋቦን)
ዩኤስኤም አልጀር (አልጄሪያ) 2-0 ሪያል ክለብ ዱ ካዲዮጎ (ቡርኪናፋሶ)
እሁድ
አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ) 2-0 ፋት ዩኒየን ስፖርት (ሞሮኮ)
ክለብ ፌሬቫያሮ ደ ቤይራ (ሞዛምቢክ) 2-0 ባራክ ያንግ ኮንትሮለር (ላይቤሪያ)
ኤሲ ሊዮፓርድስ ደ ዶሊሲ (ኮንጎ ሪፐብሊክ) 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ (ኢትዮጵያ)
ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) 1-1 ካፕስ ዩናይትድ (ዚምባቡዌ)
ኮተን ስፖርት (ካሜሮን) 1-0 ሲኤንኤፒኤስ ስፖርት (ማዳጋስካር)
ሪቨርስ ዩናይትድ (ናይጄሪያ) 3-0 ኤል ሜሪክ (ሱዳን)
ጋምቢያ ፖርትስ ኦቶሪቲ (ጋምቢያ) 1-1 ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)
ዛማሌክ (ግብፅ) 4-1 ኢንጉ ሬንጀርስ ኢንተርናሽናል (ናይጄሪያ)
ኤቷል ደ ሳህል (ቱኒዚያ) 3-0 ኤኤስ ደ ታንዳ (ኮትዲቯር)
አል ሂላል (ሱዳን) 3-0 ኤኤስ ፖር ሉዊ 2000 (ሞሪሺየስ)