” አሁን ባለው ሁኔታ እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስ ከቡና ጋር እንደምቆይ ነው የማስበው” ጋቶች ፓኖም

ጋቶች ፓኖም በኢትዮጵያ ቡና የውድድር ዘመኑ ጉዞ ላይ ወሳኝ ከሆኑ ተጫዋቾች አንዱ ሆኗል፡፡ አመዛኙን የውድድር ዘመን ቡድኑን በአምበልነት የመራው ጋቶች ኢትዮጵያ ቡና ወደ ጎንደር ተጉዞ ፋሲል ላይ የ4-1 ድል ካስመዘገበ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ከአስቸጋሪ የውድድር ዘመን ጅማሮ በኋላ ቡድናቸው እየተሻሻለ መሆኑንና በጥሩ መንገድ እየተጓዘ መሆኑን ተናግሯል፡፡

” ሁሌም ኢትዮዽያ ቡና ፕሪሚየር ሊጉን በጥሩ ሁኔታ አይጀምርም፡፡ ባለፉት አመታት በደካማ አቋም ጀምረን ከጨዋታ ጨዋታ ነው እየተሻሻልን የምንመጣው፡፡ ነገር ግን ከአምናው በተሻለ በዘንድሮ አመት ነጥቦች መሰብሰብ ችለናል፡፡ ይህ ጥሩ ነገር ነው። በሁለተኛው ዙርም በጥሩ ሁኔታ እየሄድን እንገኛለን። ቡድናችን ውስጥ ያለው ተነሳሽነት ስሜት መልካም ነው። ” የሚለው ጋቶች በወቅታዊ አቋማቸው በመዝለቅ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ጫና የማሳደር አላማ እንዳላቸው ጨምሮ ገልጿል፡፡

” ገና ብዙ ጨዋታ አለ፡፡ ዛሬ (ከፋሲል ጋር የተደረገው) እንዲህ ባለ አጨዋወት ከሜዳ ውጭ ማሸነፋችን የበለጠ ያበረታታናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተስተካካይ ጨዋታ ቢቀረውም የነጥብ ልዩነታችን 4 ሆኗል፡፡ ቀጣዩን አንድ ጨዋታም የማይጫወቱ በመሆኑ ከአዳማ ጋር ያለውን ጨዋታ ካሸነፍን የነጥብ ልዩነቱ ወደ አንድ ይጠባል፡፡ ስለዚህ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታ ቢኖረውም መሪው ላይ ጫና እናሳድርበታለን ፤ ይህ ደግሞ ለዋንጫ ለምናደርገው ፉክክር ጉዞ ጥሩ መንገድ ይሆናል።”

ኢትዮጵያ ቡና በመጀመርያዎቹ 9 ሳምንታት ያሳየውን ደካማ አቋም ተከትሎ ሰርቢያውን አሰልጣኝ ኒቦሳ ቪቼቪች አሰናብቶ በገዛኸኝ ከተማ መተካቱ ቡድኑ ላይ የውጤት ለውጥ አምጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለጋቶች የተሰጠው የማጥቃት ነጻነት ብቃተቱን አውጥቶ እንዲጠቀም አድርጎታል፡፡ ጋቶችም በለውጡ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡

” ለብዙ ጊዜያት የተከላካይ አማካይ ሆኜ ነበር የተጫወትኩት። አሁን የአጥቂ አማካይ በመሆን ወደ ፊት በመሄድ በማጥቃቱ ላይ አመዝኜ እየተጫወትኩ ነው። አሰልጣኞቹ ያመኑበትን አድርገዋል። በአጋጣሚ በቦታው ያሉት ተጨዋቾች ጉዳት ላይ መሆናቸው እኔን ወደ ፊት በመሄድ አክሊሉ በእኔ ቦታ ላይ እንዲጫወት ሆኗል። በዚህም ውጤታማ እየሆንን እንገኛለን፡፡ ጎሎችም በብዛት እያስቆጠርን እንገኛለን፡፡ እኔም ጎል እያስቆጠርኩ እገኛለው፡፡ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። ወደ ፊትም ጉዟችንን አጠናክረን በዚህ መልኩ እንቀጥላለን።” ብሏል፡፡

ጋቶች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለው ኮንትራት ለመጠናቀቅ የተቃረበ በመሆኑ በክለቡ ያለው ቆይታ አልያም ቀጣይ ማረፊያ አጓጊ ሆኗል፡፡ በቡና ውለል ከማራዘም ባሻገር ወደ አውሮፓ የመዘዋወር እድል ያገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ጋቶች ከቡና ጋር እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ እንደሚቆይ ከመግለጽ ውጪ ስለ ቀጣይ ሁኔታው ከመግለፅ ተቆጥቧል፡፡

” ቆይታዬን በተመለከተ ከቡድኑ አመራሮች ጋር በሚገባ ተነጋግሬያለው ፤ ጥሩ መግባባት ላይም ደርሰናል፡፡ እስከ ሰኔ 30 ድረስ በኢትዮዽያ ቡና እቆያለው። ከዛ በኋላ በቀጣይ የውጭ እድል አለ፡፡ ሌሎችም ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ያ ወደ ፊት ነው የሚታወቀው። አሁን ባለው ነገር ግን እስከ ውድድር አመቱ መጨረሻ ድረስ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር እንደምቆይ ነው የማስበው።” ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል፡፡

2 Comments

Leave a Reply