ቅዱስ ጊዮርጊስ ያስገነባው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ እግርኳስ አካዳሚ በይፋ ተመረቀ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር በቢሾፍቱ ከተማ ያስገነባው የይድነቃቸው ተሰማ የእግርኳስ አካዳሚ ዛሬ በይፋ ተመርቋል። በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን ፕሬዝደንት ኢሳ ሃያቱ እና የስራ አስፈጻሚ አባላት፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ጁነይዲ ባሻ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል። ከስነስርዓቱ መካሄድ አስቀድሞ ቅዳሜ እለት ቆሼ አካባቢ በተከሰተው አሳዛኝ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡

በምርቃት ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የካፍ ፕሬዝደንት ኢሳ ሃያቱ ባደረጉት ንግግር በአካዳሚው ምርቃት ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡ “ይህ አካዳሚ በይፋ በመመረቁ ደስታ ተሰምቶኛል። ለተደረገልኝ መልካም አቀባበል በጣም አመሰግናለው። የዚህ አካዳሚ መገንባት አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እግርኳስ በሃገሪቱ እንዲስፋፋ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚራምድ ይሆናል። አቶ አብነት ገብረመስቀል እና በዚህ ስራ ለተሳተፋችሁ በሙሉ ምስጋናዬ ይድረሳቸሁ። በተለይ የአካዳሚው ስያሜ ከእኔ አስቀድሞ የካፍ ፕሬዝደንት በነበረው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስያሜ መሰየሙ አስደስቶኛል፡፡ ረጅም እድሜ ለእግርኳስ እና ለኢትዮጽያ እመኛለው።” ብለዋል፡፡

የእግርኳስ አካዳሚው በ24ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው። ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ፈሰስ ተደረጎበታል የተባለው አካዳሚው 100 ታዳጊ ተጫዋቾችን መያዝ ይችላል፡፡ በውስጡም በአዳሪነት የመኖሪያ አገልግሎት የሚሰጥ፣ የተደረጃ የመመገቢያ አዳራሽ፣ የፊፋን ደረጃ ያሟሉ ሁለት የመለማመጃ እና የመጫወቻ ሜዳዎች፣ ጂምናዚየም፣ የህክምና ማዕከል፣ የአስተዳደር ክፍሎች፣ የእንግዶች ክፍል፣ የጥገና ክፍል እና መጋዘንን ያካተተ ነው፡፡ የአካዳሚውን ስያሜ ክለብ በተጫዋችነት፣ በአሰልጣኝነት እና አስተዳዳሪነት በመሩት ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስም ተሰይሟል፡፡ በስነ-ስርዓቱም ላይ የአቶ ይድነቃቸው ልጆች ተገኝተዋል፡፡

የስፖርት ማህበሩ የቦርድ ፕሬዝደንት አቶ አብነት ገብረመስቀል አካዳሚው ተተኪ ተጫዋቾችን ለማፍራት እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል፡፡ “ረጅም ጉዞ ለመጓዝ ባለን ራዕይ ዋና የትኩረት አቅጣጫችን ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት ነው፡፡ ለሀገራችን የእግርኳስ እድገት ደር ቀዳጅ የሆነና መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን በማመን ይህን ማዕከል ለማቋቋም ችለናል፡፡ ተተኪው ትውልድም በብርቱ ጥረት እና ልፋት የተገነባውን ይህንን አካዳሚ በቅርስነት ተረክቦ አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረገ ውጤታማነቱን እንደሚያስቀጠለው ሙሉ እምነት አለን፡፡” አቶ አብነት ጨምረው አካዳሚውን ለመስራት የተባበሯቸውን አካላት አመስግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ጁኒይዲ ባሻ የእንኳን ደስ አላችሁ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ “የክለቡን የአስተዳደር ሰራተኞች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩ ስም እና ዝና ያለው የኢትዮጵያ ክለብ ነው፡፡ በተለያዩ ግዜያት ኢትዮጵያን በመወከሉ የኢትዮጵያ አምባሳደር ከመሆን አልፎ የኩራትም ምንጭ ለደጋፊዎቹ መሆን ችሏል፡፡ ይህን አካዳሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ መገንባቱ ለሌሎች የኢትዮጵያ ክለቦችም የማንቂያ ደውል ነው፡፡”

የእግርኳስ አካዳሚውን ወደ ስራ ለማስገባት ቢያንስ በአመት 10 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግ የተነገረ ሲሆን የሆራይዘን ፕላንቴሽን፣ ቢጂአይ፣ ሞሃ ኢንደስትሪ እና ደርባ ሲሚንቶ አካዳሚው ራሱን እስኪችል ወጪውን ለማሸፈን ተስማምተዋል፡፡ ቢጂአይ 50 በመቶውን ወጪ ሲሸፍን ቀሪዎቹ ሶስት የሜድሮክ ድርጅቶች 50 በመቶውን እንደሚሸፍኑ ተገልጿል፡፡

Leave a Reply