የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታውን ለመከወን ወደ ኪጋሊ አምርቶ የነበረው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ምሽት ላይ አዲስ አበባ ገብቷል።
በአሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ትናንት ሩዋንዳን ገጥሞ በረድኤት አስረሳኸኝ ሁለት እንዲሁም በአረጋሽ ከልሳ እና ቱሪስት ለማ ጎሎች 4-0 በማሸነፍ ወደ ቀጣዪ የማጣርያ ዙር ለማለፍ መንገዱን የጠረገ ሲሆን በዛሬው ዕለት ምሽት አራት ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ደርሷል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን እና ም/የፅሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ ቦሌ ዓለምአቀፍ አየር ማረፍያ በመገኘትም ለልዑካን ቡድኑ አቀባበል አድርገዋል።
በአቀባበሉ ላይ የተገኙት አቶ ባህሩ ጥላሁን እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በመቀጠል አቶ ኢሳይያስ ጂራ በበኩላቸው “እንኳን ደስ አላችሁ፤ ይህን ውጤት በቀጣይ ጨዋታዎች በመድገም ብሔራዊ ቡድኑን ዓለም ዋንጫ ማድረስ እንደምንችል ከተስፋ በዘለለ በሥራ ስላሳያችሁን እናመስግናለን። መጨረሻው እንዲያምር አሁንም ጠንክረን መሥራት አለብን።” ብለዋል።
ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረገው አሰልጣኝ ፍሬው “የኢትዮጵያን ህዝብ እንኳን ደስ ያለን ማለት እፈልጋለሁ። ልጆቼ የተቻላቸውን አድርገዋል። ከዚህም በላይ ግቦች ማስቆጠርም እንችል ነበር። ይህ ውጤት ከላይ ከፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች አንስቶ እስከ ታች ድረስ እስካለነው ባልደረቦቼ እና ተጫዎቾቼ ድረስ በጋራ የመስራታችን ውጤት ነው። ተጋጣሚያችንን አጨዋወት እዛው እያየን የጨዋታ ለውጥ አድርገናል። በዚህም ውጤታማ ሆነናል። በቀጣይ ከአመራሩ ጋር በመነጋገር የወዳጅነት ጨዋታዎችን በማከናወን የበለጠ ክፍታችንንን ለመቅረፍ እንሞክራለን። በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ፈጣሪ ያክብርልኝ ማለት እፈልጋለሁ” ብሏል።
የሴቶች ከ20 ዓመት ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን በመስከረም ወር መጨረሻ በሜዳው እንደሚያከናውን ይጠበቃል።