የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ለአፍሪካ እግርኳስ እድገት ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የላበረከቱ የእግርኳስ ሰዎች ዛሬ በአፍረካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከጠቅላላ ጉባኤው መጀመር አስቀድሞ እውቅና ሰጥቷል፡፡ ሁለትም ኢትዮጵያዊያንም እውቅና በማግኘት የክብር ወርቅ ሜዳሊያን ከካፍ ፕሬዝደንት ኢሳ ሃያቱ እጅ ተቀብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የቦርድ ፕሬዝደንት አብነት ገብረመስቀል ለእግርኳሱ ባበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅናን አግኝተዋል፡፡ ጋዜጠኛ ገነነ ለረጅም አመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የሰራ አንጋፋ ጋዜጠኛ ሲሆን በሊብሮ ጋዜጣ አዘጋጅነቱ በደንብ የምታወቅ ነው፡፡ አሁን ላይ በራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅነት ስራ ላይ ይገኛል፡፡ ከአሜሪካ መልስ ቅዱስ ጊዮርጊስን የኢትዮጵያ ሃያሉ ክለብ ያደረጉት አቶ አብነት ክለቡ በተሻለ መንገድ እንዲጓዝ ለማደረግ የሰሩት ጥረት ጥሩ የሚባል ነው፡፡
እውቅናን ካገኙ ሰዎች መካከል ግብፃዊው የቀድሞ የአል አሃሊ ተጫዋች እና ፕሬዝደንት ሃሰን ሃምዲ እና ደቡብ አፍሪካዊው የእግርኳስ ኮሜንታተር ማርክ ግለሴን ይጠቀሳሉ፡፡ ሙስጠፋ ባድሪ፣ ጆሴፍ ጋቢዮ፣ አቤል ምቤንጉ፣ ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ፊሊፕ ዛግሬፍ ሎሎች እውቅናን ያገኙ ሰዎች ናቸው፡፡