ማዳጋስካራዊው አህመድ አህመድ አዲሱ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን ፕሬዝዳንት ሆነው ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት እንዲመሩ ዛሬ በጠቅላላ ጉባኤው ተመርጠዋል፡፡ አህመድ ለ28 አመታት ካፍን የመሩትን ኢሳ ሃያቱን አሸንፈው ነው በስተመጨረሻም የካፍ ፕሬዝደንት መሆን የቻሉት፡፡
ሰባት ተከታታይ ምርጫን ማሸነፍ የቻሉት ካሜሮናዊው ሃያቱ ለአህመድ እጅ ሰጥተዋል፡፡ አህመድ የ34 የካፍ አባል ፌድሬሽኖችን ድምፅ ሲያገኙ ሃያቱ 20 ድምፅን ብቻ አግኘተው ለመሸነፍ በቅተዋል፡፡ የ57 ዓመቱ አህመድ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ከወሰኑ ወዲህ በተደጋጋሚ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ተሸናፊው ሃያቱ በሙስና ቅሌት እና ክሶች በሳምንቱ መጀመሪያ የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆነው ቆይተዋል፡፡ አዲሱ ተመራጭ አህመድ በካፍ ተጠያቂነት እና ግልፅነት ለማስፈን እንደሚሰሩ ሲገልፁ ነበር፡፡ በጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግርም የካፍ አባል ሃገራትን የሚጠቅሙ ስራዎችን ለመስራት እንደሚተጉ ገልፅው ነበር፡፡ የአህመድን መመረጥ ተከትሎ በስብሰባ አዳረሹ የነበሩ የአህመድ ደጋፊዎች በከፍተኛ ደምፅ ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ አህመድ ወደላይ በማንሳትም አስገራሚ ድባብን አሳይተዋል፡፡