ከፍተኛ ሊግ | ጅማ ከተማ ምድብ ለን በመሪነት አጠናቋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 1ኛ ዙር መደበኛ ጨዋታዎች ተጠናቀው ተስተካካይ ጨዋታዎች በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ከፍተኛ ፉክክር እየተስተናገደበት በሚገኘው ምድብ ለ ሰንጠረዥ አናት ላይ በሁለት ነጥቦች ልዩነት ተከታትለው የተቀመጡት ሀላባ ከተማ እና ጅማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ ነበር፡፡ ጨዋታውን የሚያሸንፈው ቡድን መሪነቱን ለማስከበር የሚያደርጉት ፍልሚያ በመሆኑም ጠንካራ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ተጠብቆ ነበር፡፡ እንደተጠበቀውም ጨዋታው ጥሩ ፉክክር አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተፈፅሟል፡፡

ሀላባ ቁሊቶ ላይ በ9:00 ሰዓት የተጀመረው ጨዋታ በአዲሰ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ በሚባለው ቦታ ላይ ለደረሰው አደጋ ህየይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጎ ነበር የተጀመረው።

ተመጣጣኝ ፉክክር በተስተናገደበት የመጀመርያው አጋማሽ ሀላባ በ18ኛው ደቂቃ ቀዳሚ የሆነበትን ጎል በአብነት ተሾመ አማካይነት  አግኝቷል፡፡ ሆኖም ጨዋታውን በተቻላቸው መጠን ለመቆጣጠር እና ተጨማሪ ጎል እንዳይቆጠርባቸው ሲጥሩ የነበሩት ጅማዎች በ35 ደቂቃ ንጋቱ ገ/ስላሴ  አክርሮ ወደጎል  የመታወን ኳስ ጎል ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ ጅማዎች በአቅሌስያስ ግርማ ሀላባዎች ደግሞ በአቦነህ ገነቱ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ ጫና ፈጥረው የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት የቻሉት ሀላባ ከተማዎች በጅማ የሜዳ አጋማሽ ላየይ አመዝነው ሲንቀሳቀሱ የምድቡን መሪነት አስጠብቀው አንደኛውን ዙር ለማጠናቀቅ አቻ ውጤተት በቂያቸው የነበረው ጅማ ከተማዎች አፈግፍገው ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፡፡

ሀላባውች በተደጋጋሚ የጅማ ጎል ቀጠና ሲደርሱና የተሻለ ሙከራ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን በስንታየው አሸብር ፣ በተመስገን ይልማ ፣ በአብነት ተሾመ ፣ በሰይድ ግርማ እንዴሁም የቀድሞ የወላይታ ድቻ አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱ አማካኝነት ጥሩ የሚባሉ የጎል ሙከራዎች አድርገው ነበር፡፡ በተለይ በ78ኛው ደቂቃ ላይ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነትን በ14 ግቦች እየመራ የሚገኘው ዘከርያስ  ፍቅሬ በጭንቅላት ገጭቶ የውስጠኛውን የግብ አግዳሚ ለትሞ ወደውጭ የወጣው ኳስ የሚያስቆጭና አሸንፈው ሊወጡ የሚችሉበት ግሩም ሙከራ ነበር፡፡ ሀላባዎች የውስጠኛውን አግዳሚ ገጭቶ ከመስመር አልፎ በመንጠሩ ጎል ሆኖ ሊጸድቅ ይገባዋል በሚል በዳኛው ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ከዕረፍት በኋላ በእንቅስቃሴ ተበልጠው የነበሩት ጅማዎች ተቀይሮ ከገባ በኋላ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው የቀድሞ የሙገር ሲሚንቶ አማካይ አብዱልከሪም አባፎጊ አማካኝነት መልካም የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ ጨዋታውም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ጅማ ከተማ በ26 ነጥቦች የምድብ ለን በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ ሀላባ ከተማ በ24 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡

በእለቱ ዲላ ላይ በተደረገ ሌላ ተስተካካይ ጨዋታ ዲላ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሀዲያ ሆሳዕናም መሪነቱን መረከብ የሚችልበትን እድል አምክኗል፡፡

ምስጋና

ጨዋታውን ለመዘገብ ወደ ስፍራው አቅንታ የነበረው ሶከር ኢትዮጵያ በሀላባ ከተማ ለተደረገላት መልካም አቀባበል የከተማውን ህዝብ እና የሀላባ ከተማ ደጋፊዎች ለማመስገን ትወዳለች፡፡

Leave a Reply