” ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ትልቅ ደረጃ የመድረስ ህልሜን በማሳካቴ ደስተኛ ነኝ ” ሳላዲን ሰኢድ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር ኤሲ ሊዮፓርድስን 3-0 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፎ ወደ ምድብ ድልድል መግባት ችሏል፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው ጨዋታም በሳላዲን ሰኢድ ሁለት ግቦች ታግዞ 2-0 አሸንፏል፡፡ ሳላዲን ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር የመልስ ጨዋታ እንደ መሆኑ መጠን ሽንፈታቸውን ለመቀልበስ በጣም ተጭነውን ነበር። እኛም ያገኘናቸውን የጎል አጋጣሚ አለመጠቀማችን ውጥረት ውስጥ ከቶን ነበር፡፡ ያም ቢሆን ተረጋግተን በትኩረት በመጫወት ታሪክ መስራት ችለናል፡፡

ጎል አስቆጥራለው ብለህ አስበህ ነበር?

ሁሌም ቅደሚያ የምሰጠው ክለቤ አሸናፊ ሲሆን ነው ደስተኛ የምሆነው፡፡ ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ጎሎችን ሳስቆጥር ደስ ይለኛል፡፡ እንግዲህ በሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች (4 ጨዋታዎች) 5 ጎሎችን ማስቆጠሬ የበለጠ ደስተኛ ያደርገኛል፡፡

ክለብህ በታሪክ የመጀመርያ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ድልድል ውስጥ በመግባቱ ምን ተሰማህ?

በጣም ደስ ብሎኛል ከዚህ በፊትም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ትልቅ ደረጃ መድረስ እፈልግ ነበር። ያንን ህልሜን በማሳካቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከዚህም በኋላ ሌላ ታሪክ ለመስራት የበለጠ ጠንክሬ እሰራለው፡፡

ምድብ ድልድል ውስጥ ገብታችኋል፡፡ ከዚህ በኋላ ምን እንጠብቅ ?

አሁን አንዱን ከባድ ነገር ጠንክረን ሰርተን ምድብ ድልድል ውስጥ መግባትን አሳክተናል። ከዚህ በኋላ የተሻለ ውጤት ለማምጣትና ሩብ ፍጻሜውን ለመቀላቀል እናልማለን፡፡ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ደግሞ ጠንክረን እንሰራለን፡፡

በየጨዋታው ያለህ የመጫወት አቅም እና ፍላጎት አስገራሚ ነው፡፡ ይህን እንዴት ትገልፀዋለህ?

ሁሌም የሚያስጨንቀኝ ጥሩ ሆኖ መገኘት ነው። ይህ ለኔ እንጀራዬ ነው፡፡ ቤተሰቤም በዚህ ሙያ ያለፈ ነው፡፡ እኔ ስራዬን አከብራለው ፤ ሁሌም ብቁ ሆኜ ለመገኘት ጠንክሬ እሰራለው፡፡ ይህ በየጨዋታው በጥሩ ብቃት ጨርሼ እንድወጣ አግዞኛል፡፡

Leave a Reply