የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ዛሬ ሲጀመር ሲዳማ ቡና ተፈትኖም ቢሆን ድሬዳዋ ከተማን 3ለ2 ረቷል፡፡
በሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በጎፈሬ የትጥቅ አምራች ተቋም ስፖንሰር አድራጊነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ የመክፈቻ መርሀግብር ዛሬ በሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል በይፋ ተጀምሯል፡፡የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍሬው አሬራ ፣ አቶ ጥላሁን ሀሜሶ የሀዋሳ ከተማ የስፖርት ኮሚሽነር እንዲሁም አንበሴ አበበ የክልሉ እግር ኳስ ፌድሬሽን ም/ፕሬዝዳንት ሌሎች የክብር እንግዶች ተገኝተው ጨዋታውን አስጀምረውታል፡፡
እጅግ ጠንከር ባለ ዝናብ ታጅቦ የጀመረው ጨዋታ 9፡14 ሲል በፌድራል ዳኛ አብረሀም ኮይራ መሪነት ተጀምሯል፡፡ የሲዳማ ቡና ፍፁም የእንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራ ብልጫ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ያስመለከተን ገና በጊዜ ነበር፡፡5ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ በግራ በኩል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ የሰጠውን ኳስ አዲሱ ፈራሚ ፍሬው ሰለሞን ከመረብ አገናኝቶ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ የሜዳው ክፍል በአግባቡ በመጠቀም የተሳካላቸው ቡናማዎቹ በተለይ መሀል ሜዳ ላይ ፍሬው ሰለሞን እና ቴዎድሮስ ታፈሰ በሚፈጥሩት የአንድ ሁለት ቅብብል መነሻነት ወደ ሁለቱም ኮሪደሮች በተደጋጋሚ በመላክ በድሬዳዋ ላይ ጫናን ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡
7ኛው ደቂቃ በዚህ የጨዋታ መንገድ ያገኘውን ኳስ ሰለሞን ሀብቴ በግራ የድሬዳዋ የሜዳ ክፍል ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ነፃ አቋቋም ላይ ለነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ አቀብሎት አጥቂው ወደ ጎልነት ለውጧት የግብ መጠኑን ወደ ሁለት አሳድጓል፡፡ ኳስን በመቆጣጠር ብልጫን በተጋጣሚያቸው ላይ ሲያሳዩ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በቴዎድሮስ ታፈሰ እና ይገዙ ቦጋለ አማካኝነት ተጨማሪ ጎል ሊሆን የሚችል ዕድልን አግኝተው ሳየጠቀሙ ቀርተዋል፡፡ 24ኛው ደቂቃ ላይም ከመሀል ሜዳ በተጀመረ አስገራሚ የኳስ ፍሰት ከኮልፌ ለሲዳማ የፈረመው ብሩክ ሙሉጌታ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ለይገዙ ሰጥቶት ተጫዋቹም በቀላሉ ከመረብ በማዋሀድ የሲዳማ ቡናን መሪነት ወደ 3ለ0 አሸጋግሯል፡፡
በሲዳማ ቡና ለመበለጥ የተገደዱት እና የተከላካዮቻቸው የአቋቋም ስህተት በጉልህ የተስተዋለባቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በአጋማሹ የፈጠሩት የግብ ሙከራ አንድ ብቻ ነበረች፡፡ 40ኛው ደቂቃ ሙኽዲን ሙሳ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ጋዲሳ መብራቴ መቶ መክብብ ደገፉ በቀላሉ የያዘበት አጋጣሚ ብቸኛዋ ሆናለች፡፡ አጋማሹ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው ሲዳማ ቡና በሰለሞን ሀብቴ ፣ ፍሬው ሰለሞን እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ተጨማሪ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም አጋማሹ በ3 ለ0 መሪነት ተገባዷል፡፡
ምንም እንኳን የጨዋታው እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ቢታይበትም በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫን አሳይተው ሶስት ግቦችን አስቆጥረው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ተከላካዮቻቸው በሰሯቸው ስህተት የተነሳ ሁለት ግብን በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ 51ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማን ተከላካዮች ዝንጉነት የተመለከተው አብዱራህማን ሙባረክ የግል አቅሙን በሚገባ ተጠቅሞ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ የመክብብ ደገፉ የቦታ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ኳሷ ከመረብ አርፋ ድሬዳዋ ከተማን ወደ ጨዋታ መልሳለች፡፡
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ የመከላከል ስህተት ሲዳማ ቡና ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል ጋናዊው የመስመር ተከላካይ አብዱለጢፍ መሀመድ በግራ በኩል ሁለት ተጫዋቾች አልፎ ወ የሰጠውን ጋዲሳ መብራቴ በማስቆጠር ጨዋታው 3ለ2 ተሸጋግሯል፡፡
ከመጀመሪያው አጋማሽ የተቀዛቀዙት ሲዳማ ቡናዎች ከማጥቃቱ ይልቅ ወደ ኋላ አፈግፍገው ለመጫወት መሞከራቸው ግቦች ለማስተናገዳቸው ዋነኛው ምክንያት ነበረ ይሁን እንጂ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታ ሲስተም ለመግባት ጥረት ቢያደርጉም ውጤታማ ሊሆኑ ግን አልቻሉም።
በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በአቤል ከበደ እና አብዱራህማን ሙባረክ አማካኝነት አቻ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ የነበረ ቢሆንም ጨዋታው ሲዳማ ቡናን 3ለ2 አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል፡፡የዕለቱ ዳኛ ጨዋታው መጠናቀቁን የሚያበስረውን ፊሽካ ካሰሙ በኋላ የድሬዳዋው አማካይ ብሩክ ቃልቦሬ ከዳኛው ጋር በፈጠረው ንትርክ በሁለት ቢጫ የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል፡፡
ጨዋታው ፍፃሜውን ካገኘ በኋላ ጎፈሬ የሲዳማ ቡናው አማካይ ፍሬው ሰለሞን የጨዋታው ኮከብ በማለት ሸልሞታል፡፡