የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ስለ ትላንቱ ድላቸው ይናገራሉ

በቶታል ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ በመካፈል ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ የኮንጎ ሪፐብሊኩ ኤሲ ሊዮፓርድስን 3-0 በሆነ የድምር ውጤት በማሸነፍ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ የመጀመሪያው የምድብ ድልድሉን መቀላቀል የቻለ ክለብ መሆን ችሏል፡፡

ከዚህ ታሪካዊ ድል በኃላ በትላንቱ የመልስ ጨዋታ ላይ ቡድኑን በአንበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የገባው አዳነ ግርማ ፣ ዶሊሴ ላይ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ብቸኛዋን የማሸነፍያ ግብ ያስቆጠረውና በጨዋታው በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ በመሠናበቱ ምክንያት በትላንቱ የመልስ ጨዋታ ላይ መሠለፍ ያልቻለው ምንተስኖት አዳነ ፣ በጨዋታው መልካም እንቅስቃሴ ያሳዩት አስቻለው ታመነ እና ፍሬዘር ካሳ በተለይ ለሶከር ኢትዮጲያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አዳነ ግርማ

ሰለ ጨዋታው

“ሊዮፓርዶችን አይደለም በሜዳቸው እዚህም ምን ያህል ጠንካራ እንደሆኑ አሳይተዋል፡፡ ይህንን ጠንካራ ቡድን ጥለን በማለፋችን በጣም ደስተኛ ነው የሆንነው፡፡ የዛሬው ድል እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክለብ በጣም ትልቅ ድል ነው፡፡ በተለይ ለኛ የዛሬዋ ቀን እጅግ ታሪካዊ የሆነች ቀን ነች ፤ ከዚህ በፊት በብዙ አጋጣሚዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት በሀገር ውስጥ ብቻ ተገድቦ ነበር፡፡ ነገርግን በዚህ ታሪካዊ ውጤት መሠረት በአፍሪካ ከሚገኙ 16 ምርጥ ቡድኖችን ውስጥ መግባታችን ለኛ እጅግ በጣም ትልቅ ድል ነው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የ81 አመታት ጉዞ ውስጥ በጣም ታላላቅ እና ስመጥር ተጫዋቾች በተጫወቱበት በዚህ ታሪካዊ ክለብ ለዘመናት ተሞክሮ ያልተሳካውን ውጤት በዚህ የቡድን ስብስብ ይህ ታሪክ በመምጣቱ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡”

ከዚህ ቀደም ቡድኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች በቻምፒየንስ ሊጉ ወደ ወሳኝ ምእራፍ ደርሶ በጥቃቅን ስህተቶች ከጉዞው የተሰናከለባቸው አጋጣሚዎችንና የዘንድሮ ስኬት ሲነጻጸሩ

“እነዛን አስቸጋሪ ጊዜያትን ማስታወስ አልፈልግም ፤ ህይወት ትቀጥላለ፡፡ ከአንተ የሚጠበቀው ነገር ቢኖር ጠንክረህ መስራት ነው፡፡ ጠንክረን መስራታችን እነዛን አስቸጋሪ ጊዜያትን አልፈን ለዚህ ጊዜ እንድንደርስ ረድቶናል፡፡”

ስለ ደጋፊው ማራኪ ድባብ

“እኔ ይህንን ደጋፊ በምንም ቃል መግለፅ አልችልም ፤ ከቃላትም በላይ ናቸው፡፡ እንደአጠቃላይ ስለዚህ ታሪካዊ ደጋፊ ማለት የምችለው ፈጣሪ ይስጥልኝ ብቻ ነው፡፡

 ምንተስኖት አዳነ

ጨዋታን ሜዳ ውስጥ ሆኖ መጫወትና ከተመልካች ጋር ቁጭ ብሎ መታደም ያለው ልዩነት

“በሁለቱ መሀል እጅግ በጣም ሰፊ የሆነ ልዩነት አለ፡፡ በተለይም ጨዋታው እጅግ ጭንቀት የተሞላበት በመሆኑና ቡድናችን ሜዳ ላይ ጥሩ ባለመሆኑ የተነሳ ብልጫም ተወስዶብን ነበር ፤ ባለቀ ሰአት ባስቆጠርናት ግብ ነበር ይህንን ጣፋጭ ድል ያስመዘገብነው ለዛም ይመስላል በጣም ጭንቀት ውስጥ ሆኜ ነበር ጨዋታውን የተመለከትኩት፡፡”

ከዚህ ታሪክ ጀርባ ከሚወሱ ወሳኝ ተጫዋቾች አንዱ በመሆኑ ስለተሰማው ስሜት

“ይህችን ቀን ሁልጊዜም ቢሆን እንደ ተጫዋች ስንመኛት የነበረች ቀን ነች ፤ የዚህ ታሪክ አካል በተለይም በከባዱ የሜዳ ውጪ ጨዋታ ላይ ከዛሬው ይበልጥ ጠንካራ የነበረውን ኤሲ ሊዮፓርድስን በእኔ ግብ አሸንፈን ይህን የመሰለ ውጤት በማግኘታችን በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”

በቀጣይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስለሚጠበቀው ነገር

“አሁን ዋንኛው ስጋታችን የነበረው የጥሎ ማለፍ ውድድርን ተሻግረናል፡፡ ከዚህ በኃላ በምድብ ውስጥ በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ 6 ጨዋታዎች ላይ በጥንቃቄ ተጫውተን ጥሩ ነጥብ በመሰብሰብ ወደ ስምንቱ ውስጥ የምንገባ ይመስለኛል፡፡”

ስለ ክለቡ ደጋፊዎች

“ደጋፊዎቻችን በተለይም ዘንድሮ ከጨዋታ ጨዋታ የሚገርም ድባብን እየፈጠሩ ይገኛል፡፡ለእኔ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ደጋፊዎቻችን ከኛ በበለጠ ለቡድኑ ትርጉም ያለው ስራ እየሰሩ ይገኛል፡፡በቀጣይም የእነሱ በዚህ ደረጃ አስገራሚ ድባብ መፍጠራቸው ለኛ የሞራል ስንቅ ስለሚሆነን በቀጣይ ከደጋፊዎቻችን ጋር በመተጋገዝ ለተሻለ ውጤት እንሰራለን ብዬ አስባለሁ፡፡”

አስቻለው ታመነ

ስለ ትላንቱ የመልስ ጨዋታ

“ጨዋታው ምንም እንኳን በሜዳችን ቢሆንም ከተጋጣሚያችን ቡድን ጥንካሬ አንፃር በጣም ከባድ እና ፈታኝ ጨዋታ ነበር፡፡ በተለይም ከሜዳ ውጪ ተጉዘን ማሸነፋችን በህዝቡ ዘንድ ቡድኑ ቀላል ነው የሚል እሳቤን ፈጥሮ ነበር ነገርግን በጨዋታው እንዳያችሁት ቡድኑ በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ እነዛን ሁሉ ጫናዎችን ተቋቁመን ማሸነፋችን በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡”

የአምናው እና የዘንድሮውን የቡድን ስብሰብ ሲነፃፀር

“የአምናው እና የዘንድሮው የውድድር አመት የቡድን ስብስባችን በጣም የተለያዮ ነገሮች አሉት ፤ ከነዚህም መካከል የዘንድሮው ቡድን ህብረት እና አንድነቱ እጅግ የሚያስገርም ነው፡፡በአጠቃላይ የዘንድሮው ቡድን በብዙ ነገሮች ከአምናው የተሻለ ቡድን ነው፡፡”

የዚህ ታሪክ ሰሪ ቡድን አካል በመሆኑ የሚሰማው ስሜት

“እኔ በግሌ ቡድኑን ከተቀላቀልኩኝ ገና ሁለተኛ አመቴ ነው፡፡ የዚህም ፈር ቀዳጅ ታሪክ አካል በመሆኔም እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በግሌ ደግም በቀጣይ ገና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ታሪክ እሰራለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡”

በቀጣይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ምን እንጠብቅ

“እንደሚታወቀው ያለን የቡድን ስብስብ በጣም ሰፊ እንደመሆኑም አንፃር በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግም ሆነ በቻምፒየንስ ሊጉ በመተካካት ያለንን የቡድን ስብስብ በአግባቡ መጠቀም ከቻልን ከሊጉ በተጨማሪ በቻምፒየንስ ሊጉን ጥሩ ውጤት እናመጣለን፡፡”


ፍሬዘር ካሳ

ከተስፋ ቡድኑ አድጎ በአጭር ጊዜ የዚህ ታሪክ አካል መሆኑ የፈጠረበት ስሜት

“በቅድሚያ ለማንኛውም እግርኳስ ተጫዋቾች የቅዱስ ጊዮርጊስን ማልያ ለብሶ መጫወት እጅግ በጣም ትልቅ ህልም ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ በዚህ ጠንካራ ቡድን ውስጥ ከሳምንት ሳምንት በቋሚነት ለመጫወት ከባድ ፈተናዎች አሉት፡፡ ይህንን ፈተና ለማለፍ ደግም በየልምምዱ እና ጨዋታዎች ላይ በተሻለ መልኩ ራሴን እያሳደግኩኝ ተሽዬ ለመገኘት እጥራለሁ ፤ በተጨማሪ ደግሞ ነባር የቡድኑ አባላት አዳዲስ ለመጣነው ወጣት ተጫዋቾች የሚያደርጉልን ነገር እጅግ የሚያበረታታ ስለሆነ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”

በዚህ እድሜው በታላላቅ ጨዋታዎች ላይ ሀላፊነት ተሰጥቶት ስለመጫወቱ

“በቅድሚያ ለዚህ ነገር ያበቃኝ ብዬ የማስበው ያለኝ ጠንካራ የራስ መተማመን ነው ፤ ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ስትጫወት ሁሉንም ጨዋታዎች ማሸነፍ እንዳለብህ ታስባለህ ይህም ያለብህን የቤት ስራ ከፍ ያደርገዋል ከዚህ የተነሳ ሁሉንም ጨዋታዎች ለማሸነፍ ስትል ያለህን ሁሉ ሰጥተህ እንድትጫወት ያደርግሃል፡፡”

በቀጣይ ከፍሬዘር ካሳ ምን እንጠብቅ

“እስካሁን ድረስ ለቡድኔ የተወሰኑ ጨዋታዎችን አደረኩኝ እንጂ ምንም ይህ ነው የሚባል ነገር አላደረግኩም ፤ በቀጣይ ብዙ ነገሮችን ለቡድኔ ማድረግ ይጠበቅብኛል እኔም በቀጣይ ጠንክሬ በመስራት ያለኝን ሁሉ ሰጥቼ ቡድኔን ከዚህ በተሻለ የመጥቀም ፍላጎቱ አለኝ፡፡”

በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ምድብ ድልድል የተቀላቀለው ቡድን አካል ስለመሆኑ

“በመጀመሪያ የዚህ ታሪክ ሰሪ ቡድን አባል በመሆኔ እድለኛ ነኝ በመቀጠል የዚህ ታሪክ አካል መሆኔ ያልጠበኩትን ደስታ ነው የፈጠረብኝ ፤ በጠንካራ ስራ እና በፈጣሪ እርዳታ እዚህ በመድረሳችን በጣም ደስ ብሎኛል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *