ሁለት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች ለዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ተጠርተዋል

ዩጋንዳ በመጪው ሐሙስ ከኬንያ ጋር በናይሮቢ ላለባት የአለማቀፍ የወዳጅነት ጨዋታ ሰርቢያዊው የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ 18 ተጫዋቾችን ጠርተዋል፡፡ ሚቾ በስብስባቸው ውስጥ ለጅማ አባ ቡና የሚጫወተውን ክሪቪስቶም ንታምቢ እና የቅዱስ ጊዮርጊሱን ያስር ሙገርዋን አካተዋል፡፡

ክሪቪስቶም ንታምቢ ለምዕራብ ኢትዮጵያው ክለብ ጅማ አባ ቡና በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከፈረመ ወዲህ ለቡድኑ የተሻለ ግልጋሎትን እየሰጠ ይገኛል፡፡ አማካዩ በፕሪምየር ሊጉ አንድ ግብን ማስቆጠር ሲችል በወጥነት ቡድኑን ካገለገሉ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ሚቾም የተጫዋቹን በአባ ቡና ያለውን የመጀመሪያ አመት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ተከትሎ ከኬንያ ጋር ላለባቸው የወዳጅነት ጨዋታ ጠርተውታል፡፡

የፈረሰኞቹ አማካይ ያስር ሙገርዋ ሌላው ጥሪ የደረሰው ተጫዋቾች ነው፡፡ ሙገርዋ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኮንጎ ሪፐብሊኩን ኤሲ ሊዮፓርድስን 2-0 ባሸነፈበት የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ አዳነ ግርማን ተክቶ ለጥቂት ደቂቃዎች መጫወት ችሏል፡፡ ሙገርዋ ምንም እንኳን በዘንድሮው አመት አብዛኛውን ግዜውን በተቀያሪ ወንበር ላይ ቢያሳልፍም ለኬንያው ጨዋታ ተጠርቷል፡፡

ሚቾ ለክሬንሶቹ ወሳኝ ናቸው የሚባሉ ተጫዋቾችን በስብስባቸው አላካተቱም፡፡ በጨዋታው ከዚህ ቀደም ያልተመለከቷቸውን ተጫዋቾች ለማየት እንዲረዳቸውም ከዩጋንዳ አዛም ፕሪምየር ሊግ በርካታ ተጫዋቾችን መርጠዋል፡፡ ዩጋንዳ ላለባት የአለም ዋንጫ፣ የቻን እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከወዲሁ ጠንካራ ዝግጅት ለማድረግ እንዲረዳት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ አቅዳለች፡፡

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ቤንጃሚን ኦቻን (ኬሲሲኤ)፣ ኢስማኤል ዋቴንጋ (ቫይፐርስ)

ተከላካዮች

ኒኮላስ ዋዳዳ (ቫይፐርስ)፣ ቲሞቲ አዎኒ (ኬሲሲኤ)፣ ሃቢብ ካቩማ (ኬሲሲኤ)፣ ጁኮ ሙሪሺድ (ሲምባ/ታንዛኒያ)፣  ሻፊቅ ባታምቡዝ (ተስካር/ኬንያ)፣ ጎድፍሬ ዋሉሲምቢ (ጎር ማሂያ/ኬንያ)

አማካዮች

ሃሰን ዋሳዋ (ኒጅመህ/ሊባኖስ)፣ ክሪዝስቶም ንታምቢ (ጅማ አባ ቡና/ኢትዮጵያ)፣ ያስር ሙገርዋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ/ኢትዮጵያ)፣ ሞሰስ ዋሲዋ (ቫይፐርስ)፣ ሙዛሚል ሙትያባ (ኬሲሲኤ)፣ ጆሴፍ ኦቻያ (ኬሲሲኤ)፣ ብሪያን ማጅዊጋ (ኬሲሲኤ)

አጥቂዎች

ጆኦፍሪ ሴሬንኩማ (ኬሲሲኤ)፣ ኢማኑኤል ኦክዊ (ቪላ)፣ ሚልተን ካሪሳ (ቫይፐርስ)

Leave a Reply