የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ተጀምሯል፡፡ በምድብ ሀ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመመራት ተነስቶ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፓርት አካዳሚን ሲረታ በምድብ ለ አዲስአበባ ከተማ ባለፈው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ የደረሰበትን ሽንፈት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ላይ አወራርዷል፡፡
የአበበ ቢቂላ ስታድየም ለእድሳት በመዘጋቱ ምክንያት በፕሮግራም ለውጦች እየታመሰ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ሊግ 5:00 ላይ የተገናኙት ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነበሩ፡፡ በጨዋታውም ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር የታየ ሲሆን በውጤቱም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመመራት ተነስተው 2-1 ማሸነፍ ችለዋል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ ይመችሽ ዘውዴ ባስቆጠረችው ግሩም የመልሶ ማጥቃት ግብ አካዳሚዎች እየመሩ ወደ እረፍት መውጣት ችለው ነበር፡፡
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር በታየበት የሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡
የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ደስታ የሁለተኛው አጋማሽ ቅያሬዎች ፍሬ አፍርቶ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይረው የገቡት ቤዛዊት ግዛው እና አይናለም ፀጋዬ በተከታታይ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ጨዋታውን አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል፡፡ በጨዋታው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፓርት አካዳሚዎቹ ግብ ጠባቂዋ ከንባቴ ከተሌ እና አጥቂዋ ነብያት ሀጎስ ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል፡፡
በውጤቱ መሠረት ኢትዮ ኤሌክትሪክ መከላከያ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታቸውን እስኪያደርጉ ድረስ ነጥቡን ወደ 23 ከፍ አድርጎ በ3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል፡፡
[table id=237 /]
[league_table 18073]
አመሻሽ 11፡00 ላይ በተካሄደው የእለቱ ሌላኛው መርሃግብር በምድብ ለ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ሀዋሳ አቅንቶ ከደረሰበት የ6-0 ሽንፈት አገግሞ በምድቡ ግርጌ የሚገኘው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማን በተመሳሳይ የ6-0 ውጤት አሸንፎ የባለፈው ሳምንቱን ሽንፈት ማስረሳት ችለዋል፡፡
የአዲስአበባ ከተማዎች ፍፁም የበላይነት በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በአዲስ አበባ ከተማ የ5-0 የበላይነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ ግቦቹንም ሳራ ነብሶ ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር አስራት አለሙ ፣ እታገኝ ሰይፉ እና ተራማጅ ተስፋዬ አንዳንድ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ አቃቂዎች በመጠኑም ቢሆን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ሳይሰምር ቀርቷል፡፡ ቱቱ በላይ ያሻማችውን የቅጣት ምት ኳስም አስናቀች ትቤሶ በግንባሯ ገጭታ ስትሞክር የአቃቂዋ ተከላካይ በራስ ግብ ላይ አስቆጥራ ጨዋታው በአዲስአበባ ከተማ የ6-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የዛሬው ድል ተከትሎ አዲስአበባ ከተማ ሲዳማ ቡና በመጪው አርብ ጨዋታውን እስኪያደርግ ድረስ ነጥቡን ወደ 19ከፍ አድርጎ በ5ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡
[table id=241 /]
[league_table 18083]