ጋቶች ፓኖም በኢትዮጵያ ቡና የሚያቆየውን የአጭር ግዜ ውል ፈረመ

ኢትዮጵያ ቡና አማካዩ ጋቶች ፓኖምን እስከውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በሚቆይ የሶስት ወር ውል ለማቆየት መስማማቱ ታውቋል፡፡

የጋቶች ወኪል ዴቪድ በሻ አማካዩ በቡናማዎቹ መለያ ለተጨማሪ ሶስት ወራት እንደምንመለከተው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

የጋቶች ውል መጋቢት 30 የሚያበቃ በመሆኑ ተጫዋቹ እና ኢትዮጵያ ቡና ለረጅም ሳምንታት የፈጀ ድርድር ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ከሰመኑ መፍትሄ ይበጅለታል ተብሎ የተጠበቀው የውል ማረዘሚያ ጉዳይ ዕረቡ እለት ጋቶች በይፋዊ ግል የፉስቡክ ገፅ ላይ ባሰፈረው የመሰናበቺያ ደብዳቤ ምክንያት አደገኞቹን የሚለቅ ቢመስልም ክለቡ ዛሬ ባደረገው ጥረት ወሳኙን አማካይ ለተጨማሪ ሶስት ወራት ማቆየቱን አረጋግጧል፡፡

ጋቶች በፕሪምየር ሊጉ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር ከቡድን አጋሩ ሳሙኤል ሳኑሚ ጋር በጣምራ የቡድኑ ኮከብ ግብ አግቢ ነው፡፡ በስድስት አመት የክለቡ ቆይታም ቁልፍ መሆን ከቻሉ ተጫዋቾች መካከል ይመደባል፡፡ በዝነኛው አሰልጣኝ ስዩም አባተ መልማይነት ከጋምቤላ የተገኘው ጋቶች በኢትዮጵያ ቡና መቆየቱ ሁለቱንም አካላት ደስተኛ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply