“በፌድሬሽኑ ህግ ምክንያት የጋቶችን ውል አንድ አመት አድርገነዋል” ዴቪድ በሻ

ኢትዮጵያ ቡና እና ጋቶች ፓኖም የአጭር ግዜ የውል ስምምነት መፈጸማቸው ቢረጋገጥም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የተጫዋቾች ዝውውር ህግ መሰረት የውል ግዜው ላይ ከደቂቃዎች በፊት ለውጥ መደረጉን የአመካዩ ወኪል ዴቪድ በሻ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የተጫዋቾች ደረጃ እና ዝውውር መመሪያ አንቀፅ 13 ንዑስ አንቀፅ 13.4.5 እንሚደነግገው ከሆነ ‘አንድ ተጫዋች እና አንድ ክለብ በሚያደርጉት የዝውውር የውል ስምምነት ውስጥ የጊዜ ገደቡን ወይም መጠን በስምምነት ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የውል ዘመን ከአንድ ዓመት ማነስ ከአምስት ዓመት መብለጥ የለበትም፡፡’ ይላል፡፡ መመሪያው ተከትሎ ተጫዋቹ እና ኢትዮጵያ ቡና የተዋዋሉት የሶስት ወር ግዜ ህጋዊ ባለመሆኑ ከፌድሬሽኑ ጋር በተደረገ ውይይት ወደ አንድ ዓመት ሊለወጥ ችሏል፡፡

ዴቪድ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ከሆነ ውሉ በመጀመሪያ ለሶስት ወር ብቻ ነበር፡፡ “በመጀመሪያ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተስማማነው እስከዓመቱ መጨረሻ ለሶስት ወር በሚቆይ የውል ግዜ ነበር፡፡ ፌድሬሽን ሂደን በምንፈርምበት ወቅት ፌድሬሽኑ ይህ የውል ግዜ መመሪያውን አለመከተሉን ስላስረዱን ውይይት ተደርጎ ወደ አንድ ዓመት ተለውጧል፡፡ በፌድሬሽኑ ህግ ምክንያት የጋቶችን ውል ወደ አንድ አመት አድርገነዋል፡፡ ነገር ግን ውሉ ላይ ከውል ግዜው መጨመር የተለየ የተለወጠ ነገር የለም፡፡”

ኢትዮጵያ ቡና እና ጋቶች በሳምንቱ መጀመሪያ አንስቶ በውል ማራዘሚያ ጉዳይ ምክንያት የብዙዎች መነጋገሪያ ሆነው ሰንብተዋል፡፡

Leave a Reply