በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ፈረሰኞቹ ከታሪካዊዉ የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ድል ማግስት በጦሩ የ2-1 ሽንፈትን አስተናግደዋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙበት 11 ተጫዋቾች በዛሬው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ያልነበረውን በሀይሉ አሰፋን በአቡበከር ሳኒ እንዲሁም ሮበርት ኦዶንካራን በዘሪሁን ታደለ ብቻ ተክተው ለወትሮው በሚጠቀሙበት የ4-3-3 የጨዋታ ቅርፅ ወደ ጨዋታው ሲገቡ መከላከያዎች በተለመደው የ4-4-2 ቅርፅ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ የተጠቀሙበት ተመሳሳይ 11 ተጫዋቾችን ተጠቅመዋል፡፡
በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች መከላከያዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን መውሰድ ችለዋል፡፡ ለወትሮው የመከላከያ ጠንካራ ጎን እንደነበር የሚነገርለት ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ከመከላከሉ ባሻገር በማጥቃት ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ በዛሬው ጨዋታ ላይ ግን ተገማች የሆነውን ፈጣኑን የጊዮርጊስ የመስመር አጨዋወት ለማክሸፍ በሚመስል መልኩ ከወትሮው በተለየ እንቅስቃሴያቸው በራሳቸው የሜዳ ክልል ላይ ብቻ ተገድቦ ተስተውሏል፡፡
በፈረሰኞቹ በኩል በጉዳት በዛሬው ጨዋታ ካልተሰለፈው በሀይሉ አሰፋ ያገኝ የነበሩትን ግልጋሎት አለማግኘታቸው እንደጎዳቸው ተስተውሏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በንጽጽር ጥሩ ጥሩ የግብ እድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይም አዳነ ግርማ በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት መቶ አቤል ማሞ ያዳነበትና በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ አቡበከር ሳኒ ከማእዘን የተሻገረለትን ግልጽ የማግባት አጋጣሚ ያመከነበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ፕሪንስ ሲቨሬን ተክቶ የገባው ኮትዲቯራዊው የመሀል ሜዳ ተጫዋች አብዱልከሪም ኒኪማ በ52ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር አጥብቦ በመግባት ከ16ከ50 ውጪ አክርሮ በመምታት ማራኪ ግብን አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡
ነገርግን የፈረሰኞቹ መሪነት መዝለቅ የቻለው ለ10 ያክል ደቂቃዎች ብቻ ነበር ከግቧ መቆጠር በኃላ በተደጋጋሚ ጫና መፍጠር የቻሉት መከላከያዎች በ58ተኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ደስታ ከግራ መስመር ያሻማውን የማእዘን ምት አዲስ ተስፋዬ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡
በግቧ የተነቃቁ የሚመስሉት መከላከያዎች ዳግም በ62ተኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል ሜዳ የተላከለትን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የዘሪሁን ታደለና የተከላካዮችን አለመናበብ ተከትሎ ያገኛትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ የጨዋታውን ብልጫ የወሰዱት ፈረሰኞቹ በስታዲየሙ እየጣለ የነበረው ከባድ ዝናብ ባልበገራቸው ጠንካራ ደጋፊዎቻቸው ታግዘው የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በዚህም ውጤት መሠረት መከላከያ ከታህሳስ 22 በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ድል አድርጎ በ24 ነጥብ በ8ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል በአንጻሩ ተሸናፊዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀራቸው ከተከታያቸው ደደቢት በ1 ነጥብ ከፍ ብለው አሁንም በ35 ነጥብ ሊጉን ከአናት ሆነው ይመራሉ፡፡