ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የንግድ ባንክን ያለመሸነፍ ጉዞ በሀዋሳ ከተማ ተገቷል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንትና እና ዛሬ በተካሄዱ ጨዋታዎች ፍጻሜውን ሲያገኝ በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሳይጠበቅ በተከታዩ ሀዋሳ ከተማ ሲሸነፍ ድሬዳዋ ከተማና ሲዳማ ቡና ከሜዳቸው ውጪ ወሳኝ ድልን አስመዝግበዋል፡፡

ከተያዘለት የ5፡00 መርሃግብር በ2 ሰአት ቀድሞ በተጀመረው የኢትዮጵያ ቡና እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ የ2-1 የበላይነት ተጠናቋል፡፡ ድሬዳዋ ከተማዎች ከዚህ ወሳኝ የሜዳ ውጭ ድል በኃላ ነጥባቸውን ወደ 23 አሳድገው በምድብ ሀ በአራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል፡፡

ዛሬ ረፋድ በተካሄደው የሳምንቱ ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ በሀዋሳ ከተማ ሳይጠበቅ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጲያ ንግድ ባንኮች ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ቢገኙም በተደጋጋሚ ያገኙትን የግብ ማግባት አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻሉም፡፡ በተለይም ብዙነሽ ሲሳይ እንዲሁም ሂወት ዳንጌሶ ያመከኗቸው አጋጣሚዎች ተቀጣሽ ነበሩ፡፡ በአንጻሩ ሀዋሳ ከተማዎች በጨዋታው በአመዛኙ ወደ ኃላ አፈግፍገው ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡

የተጠበቀውን ያህል ሳቢ ፉክክር ባልታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች በ72ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየችው ምርቃት ፈለቀ ከግብ ክልል ውጪ አክርራ በመምታት ባስቆጠረችው ማራኪ ግብ ሀዋሳዎች አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡

በዚህም ውጤት መሠረት ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ምድብ ለ በውድድር ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ሽንፈትን ቢያስተናግዱም አሁንም ምድባቸውን በ34 ነጥብ ይመራሉ ፤ ሀዋሳዎችም ከመሪው ንግድ ባንክ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዮነት ወደ 4 አጥብበው በ30 ነጥብ በ2ኛ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

በሳምንቱ የመጨረሻ መርሃግብር ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርስቲ በሲዳማ ቡና የ4-1 ሽንፈት አስተናግዷል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ተሽለው መንቀሳቀስ የቻሉት ቅድስተ ማርያም ዮኒቨርስቲዎች እድላዊት ለማ ባስቆጠረችው ግብ መምራት ቢችሉም ከግቧ መቆጠር በኃላ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ከመመራት ተነስተው ማሸነፍ ችለዋል፡፡

በጨዋታው የተሻለ መንቀሳቀስ ለቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ቱሪስት ፣ ገለሜ ፣ ረድኤት እና ፀሀይነሽ ግቦቹን ማስቆጠር ችለዋል፡፡ በዚህም ውጤት መሠረት ሲዳማ ቡናዎች ነጥባቸውን ወደ 19 ከፍ አድርገው በምድብ ለ በ5ተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል፡፡

[table id=237 /]

[league_table 18073]



[table id=241 /]

[league_table 18083]

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *