“ጠንካራውን ፋሲል በእርግጠኝነት ከማክሰኞው ጨዋታ ጀምሮ እንመለከታለን”- ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ 

ፋሲል ከተማ የ2008 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን ሆኖ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ከተቀላቀለ ወዲህ በሊጉ አንደኛ ዙር መልካም ጉዞ አድርጎ የውድድር ዘመኑ ክስተት መሆን ችሎ ነበር፡፡ ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ በኋላ ግን ነገሮች ለፋሲል ቀላል አልሆኑም፡፡ በ3 ጨዋታዎች ሁሉንም ሲሸነፍ 9 ግቦችንም አስተናግዷል፡፡ የቡድኑ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ከክለባቸው የሁለተኛ ዙር አቋም ጋር በተያያዘ ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

በተከታታይ ነጥብ ስለጣሉባቸው ጨዋታዎች

“እንደ ቡድን በመጀመሪያው ዙር የነበሩት መልካም ጎኖች የሆኑት የግብ እድሎችን መፍጠር እና ተጭነን በመጫወቱ በኩል አሁንም ከቡድኑ ጋር እንዳሉ ናቸው፡፡ እንደውም በየጨዋታው እየፈጠርናቸው ካሉ እድሎች አንጻር ጎሎችን ማስቆጠር ብንችል ኖሮ ይህንን ነገር ዛሬ ላይ ሆነን ባላወራንበት ነበር፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን የሚሰማኝ የቡድኑ ጠንካራ ጎኖች አሁንም ከቡድኑ ጋር እንዳሉ ነው፡፡ በቀጣይ ጨዋታዎችን አሸንፈን ወደ ነበረን ስሜት ለመመለስ እንጥራለን፡፡”

ስለ ተደጋጋሚው ሽንፈት መንስኤዎች

“እንደ ምክንያት ይህ ነው ብለን የምናስቀምጠቀው ነገር የለም ፤ እንደ እድል ሆኖ ሁለት ጨዋታዎችን በሜዳችን ነጥብ ይዘን መውጣት ሲገባን ነጥብ ጥለናል፡፡ እኛ እንደምክንያት የምናስቀምጠው እኛው ራሳችንን ነው፡፡ ምናልባት እንደሚታየው ግልፅ የሆነ የቡድን ስብስብ ጥልቀት ችግር አለብን ፤ ለምሳሌ ከከፍተኛ ሊግ ያስመጣናቸው እንደነ ሰኢድ ሁሴን ያሉ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ከማድረግ የተነሳ በሁለተኛው ዙር አቅማቸው እየተካደመ ይገኛል፡፡ በዚህም እሱን እና ሌሎች ድካም የሚታይባቸውን ተጫዋቾች መጠነኛ እረፍት ሰጥተናቸዋል ፤ ምናልባት መነሳት ካለበት ይህ የቡድን ስብስብ ጥልቀት ችግር ነው እንጂ ተወቃሾቹ እኛው እራሳችን ነን፡፡”

በውድድር ዘመኑ አጋማሽ በገበያው ላይ ንቁ ተሳትፎ ስላለማድረጋቸው

“ወደ ገበያው ገብተን ከተወሰኑ ተጫዋቾች ጋር ግንኙነት ፈጥረን ነበር፡፡ ነገርግን ክለቦቹ አብዛኛውን ሂደት ካጠናቀቅን በኃላ ልጆቹን ያስቀሩብን ሆኔታ ነው የነበረው፡፡ ከፕሪምየር ሊጉ አልፎ እስከ ከፍተኛ ሊግ ድረስ ወርደን ተጫዋቾችን ለማግኘት ጥረት አድርገን ነበር ነገርግን ያም አልተሳካም፡፡”

ወደ አሸናፊነት ስለመመለስ

“ቡድናችን በተደጋጋሚ በጫና ውስጥ ሆኖ ጨዋታቸውን እንደማድረጉ ይፈልግ የነበረው የስነ ልቦና ስራ ነበር ፤ በዚህም በደንብ ተዘጋጅተናል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ያየነውን ጠንካራውን ፋሲልን በእርግጠኝነት ከማክሰኞው የወልዲያ ጨዋታ ጀምሮ እንመለከታለን፡፡”

ጫና ውስጥ ስለመገኘትና ቡድኑ በእቅድ መሠረት እየሄደ ስለመሆኑ

“ከጫና ነፃ ነኝ፡፡ ምንም አይነት ጫና የለብኝም እኔ እንደውም ከግምት በላይ የሚያሸልም ስራ እየሰራሁ እንዳለው ነው የማስበው ፤ ስለዚህ በፍፁም ጫና ውስጥ አይደለሁም፡፡ እንደ እቅዳችን ዋንጫ ቢመጣ ማንም አይጠላም ፤ ከዋንጫ ማንሳት ጋር በተያያዘ ያለው የደጋፊዎችን ስሜት እረዳለሁ ፤ ነገርግን ማናቸውም ቢሆኑ ከእኔ የተሻለ ፍላጎት አልነበራቸውም ፤ ምክንያቱም ዋንጫ ብናመጣ የመጀመሪያው ተጠቃሚ እኔው ነኝ፡፡ ነገርግን እግርኳስ እስከሆነ ድረስ አሁንም ድረስ ውድድር ውስጥ አለን ስለዚህም እስከ መጨረሻው ድረስ እንታገላለን፡፡”

Leave a Reply