በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት መርሃግብር ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል በተባለለት ጨዋታ በ15 ነጥብ 15ኛ ላይ የሚገኘውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክንና በ12 ነጥብ በሊጉ ግርጌ የሚገኘውን አዲስአበባ ከተማን ባገናኘው ጨዋታ አዲስአበባ ከተማ 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኃላ ከሊጉ ግርጌ ተላቋል፡፡
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባሳለፍነው ሰኞ ከተጠቀሙበት 11 ተጫዋቾች ወስጥ የግራ ተከላካይ ስፍራ ላይ ሳሙኤል ዮሀንስን በአንተነህ ገ/ክርስቶስ አማካይ ስፍራ ላይ የነበረውን ዮናስ ገረመውን በአጥቂው አቢኮዮ ሻኪሩ እንዲሁም በውድድሩ ዘመን አጋማሽ ምንም ጨዋታ ሳያደርግ ጅማ አባቡናን ለቆ ወደ ቀድሞ ቤቱ የተመለሰው አጥቂው ቢኒያም አሰፋ ፒተር ንዋድኬን ተክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በቋሚ 11 መግባት ችለው ነበር፡፡
በአንጻሩ አዲስአበባ ከተማዎች ከሰኞው ጨዋታ በተለየ የ3 ተጫዋቾችን ቅያሬ አድርገው ወደ ጨዋታ የገቡ ሲሆን በዚህም መሠረት ተከላካይ ስፍራ ላይ አዳነ በላይነህ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ጨዋታውን ሲጀምር አማካይ ላይ ዘሪሁን ብርሃኑ እና ዳዊት ማሞ ወደ ቀደመ ቦታቸው ተመልሰው ቡድኑ በተመሳሳይ 4-4-2 ቅርፅ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡
በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ ሲምክሩ ተስተውሏል በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ በዘንድሮው የውድድር አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በፉክክር ጨዋታ ላይ ወደ ሜዳ የገባው ቢኒያም አሰፋ በተለይ በግሉ ጥረቶችን ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡
በ19ኛው ደቂቃ ላይ አዲስአበባ ከተማዎች በጥሩ ሆኔታ ተመስርቶ የመጣውን ኳስ ከጉዳት ተመልሶ በዛሬው ጨዋታ ወደ ቋሚነት የተመለሰው ዳዊት ማሞ በግሩም ሆኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡
ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር በመጠኑም ጥቂት ተስፋ ሰጪ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ደካማ የሆነ እንቅስቃሴ ተስተዋሎበታል፡፡
በእንቅስቃሴ ረገድ በመጀመሪያው አጋማሽ ወረድ ብለው የተስተዋሉት አዲስአበባ ከተማዎች በሁለት አጋጣሚዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተገኙትን ኳሶች ፍቃዱ አለሙ በሚያስገርም ሆኒታ ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጲያ ንግድ ባንኮች ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ሞክሯት የውጪኛውን መረብ ታካ ከወጣችው ኳስ ውጪ ይህ ነው የሚባል ኢላማውን የጠበቀ መከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርቷል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ አማካዮን ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን አስወጥተው ግዙፉን ናይጄሪያዊ አጥቂ ፒተር ንዋድኬን በማስገባት በሶስት አጥቂዎች ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ 56ተኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ተገጭቶ ሲመለስ ያገኘውን ኳስ ሀይሌ እሸቱ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ 2-0 ማስፉት ችሏል፡፡
ከሁለተኛዋ ግብ መቆጠር በተሻለ ወደፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ንግድ ባንኮች በ73ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር የተሻማለትን ኳስ ሻኪሩ ወደ ግብ ቢሞክርም ተክለማርያም ሻንቆ በጥሩ ሆኔታ አድኖበታል፡፡
በ81ኛው ደቂቃ ላይ ግዙፉ ናይጄሪያዊ አጥቂ ፒተር ንዋድኬ በረጅሙ የወረወረውን የእጅ ውርወራ ቢኒያም አሰፋ በደረቱ ካበረደ በኃላ በማራኪ ሆኒታ ተገልብጦ በማስቆጠር ቡድኑን ከባዶ መሸነፍ ያዳነችውን ግብ አስቆጥሯል፡፡ በቀሩት ደቂቃዎች አዲስአበባ ከተማዎች ሰአት በማባከንና በጥልቀት በመከላከል ውጤቱን አስጠብቀው መውጣት ችለዋል፡፡
በዚህ ውጤት መሠረት አዲስአበባ ከተማዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ላይ ድል ባስመዘገቡበት ጨዋታ ምክንያት በሊጉ ያስመዘገቡትን ድል ወደ ሶስት አሳድገው በ15 ነጥብ ከረጅም ጊዜ በኃላ የሊጉን ግርጌ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስረክበዋል፡፡