በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት መርሃግብር በተጠባቂው ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ ከሰሞኑ ጫና እየበረከተባቸው የሚገኙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ለጊዜው ቢሆን እፎይ ያሉበትን ድል ወላይታ ድቻ ላይ አስመዝግበዋል፡፡
የጨዋታው አስፈላጊነት የተረዱት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ በኩል የተሻሉ ነበሩ ፤ ነገርግን ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በአንጻሩ ወላይታ ድቻዎች ከዚህ ቀደም ከሜዳ ውጭ ሲጫወቱ እንደሚያደርጉት በጥልቀት ወደ ኃላ ተስበው በመከላከል ላይ ተጠምደው ተስተውሏል፡፡
በ21ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳንኤል ያሻማውን የማእዘን ምት በወላይታው ድቻው ግብጠባቂ የሆነው ወንደሰን ገረመው ስህተት ታክሎበት በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቡድኑን ከኢትዮጵያ መድን የተቀላቀለው ሀብታሙ ወልዴ ደገፍ በማድረግ አስቆጥሮ ድሬን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡
በወላይታ ድቻዎች በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ከድሬዳዋ ከተማ በውሰት ውል ወላይታ ድቻን የተቀላቀለው አሳምነው አንጀሎ ካደረጋት የግብ ሙከራ ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ከወትሮው በተሻለ የውጤቱን አስፈላጊነት የተረዱት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ ከወትሮው በተለየ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ ወላይታ ድቻዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በማሰብ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ በአንጻሩ አሰልጣኝ ዘላለም የአጥቂዎችን ቁጥር በመቀነስ ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡
77ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ሜዳ ተቀይሮ የገባው ሚካኤል ለማ የድሬዳዋን መሪነት ወደ አስተማማኝ የቀየረች ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ኢንተርናሽናል አልቢትር ባምላክ ተሠማ በዋና ዳኝነት በመሩት በዚህ ጨዋታ ላይ 1 ቢጫ ካርድ ብቻ ተመዟል ፤ ጨዋታውን በርካታ ቆጥር ያለው የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ ተከታትሎታል፡፡
ድሉን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 21 አሳድገው በነበሩበት የ14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀጥሉ ሌላኛው በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከዚህ በፊት የነበረው ጥንካሬ የከዳቸው ወላይታ ድቻዎች በ22 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡