የኢትዮ-አሜሪካዊው አማካይ ኢያሱ በቀለ ወደ ቡልጋሪያው ሶስተኛ ዲቪዚዮን ክለብ በስድስት ወር ውል ማምራቱ ታውቋል፡፡ የተጫዋቹ ወኪል ስቲቨን ሄኒንግ ዝውውሩን በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ አብስሯል፡፡
ኢያሱ በዓመቱ መጀመሪያ ከአሜሪካ መልስ ደደቢትን ተቀላቅሎ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ መጫወት ችሏል፡፡ አማካዩ በፕሪምየር ሊጉ እንደዚሁ ለሰማያዊዎቹ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ መጫወት ችሏል፡፡ የ24 ዓመቱ ኢያሱ በቡልጋሪያ ሶስተኛ ዲቪዚዮን ለሚወዳደረው ካሊያክራ ካቫርና ፊርማውን ያኖረ ሲሆን ውሉ እሰከ አንድ አመት መራዘም ይችላልም ተብሏል። ኢያሱ አዲሱን ክለቡን ለመቀላቀል እሁድ ማምሻውን ወደ ቡልጋሪያ አቅንቷል፡፡ በዝውውሩ መሳካትም ሄኒንግ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡
64 ክለቦች በሚሳተፉበት የሶስተኛ ዲቪዚዮን በሰሜን ምስራቅ ቪ ምድብ የሚወዳደረው ካሊያክራ ካቫርና 5000 ተመልካች በሚይዘው ካቫርና ስታዲየም ላይ ይጫወታል፡፡ ክለቡ ምስረታውን በ1922 ያደረገ ሲሆን በ1980ዎቹ እሰከሁለተኛ ዲቪዚዮን መጫወት ችሏል፡፡ በ2017 ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች አንድ ግዜ ብቻ ሲያሸንፍ በሶስት ጨዋታዎች ሽንፈትን ቀምሷል፡፡
የተጫዋቾች ወኪል የሆነው ሄኒንግ ከቀድሞ ተጫዋቾች ዴቪድ በሻ ጋር በፈጠረው ግንኙነት ወጣት ኢትዮጵያዊያን ወደ አውሮፓ ሃገራት የማዛወርን እቅዱን ከዚህ ቀደም ለሶከር ኢትዮጵያ መግለፁ ይታወሳል፡፡