የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዳሰሳ – ምድብ ሀ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አንደኛ ዙር ተገባዶ ክለቦች ሁለተኛውን ዙር ለመጀመር እየተሰናዱ ይገኛሉ፡፡ በሁለት ምድብ ተከፍሎ እየተደረገ የሚገኘው ውድድር ሁለተኛ ዙር በመጪው ሳምንት የሚጀመር ሲሆን የምድቦቹን የአንደኛ ዙር እንቅስቃሴ እና የሁለተኛ ዙር ጉዞ እንዲሁ የአሰልጣኞችን አስተያየት አካተን ያሰናዳነውን ፅሁፍ በሁለት ክፍል እናቀርብላችኀለን፡፡ በዚህ ፅሁፍም የምድብ ሀ ን  እንቃኛለን፡፡

 

ጥቂት ክለቦችን በመሪነት ፉክክሩ ያሳተፈው የምድብ ሀ

የመጀመርያዎቹ 10 ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን ስንመለከት ከምድብ ሀ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የሚያልፈው ክለብ በፍጥነት የሚታወቅ መስሎ ነበር፡፡ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአስገራሚ ግስጋሴ የምድቡን መሪነት በርቀት መምራት ቢጀምርም በመጨረሻዎቹ የ1ኛ ዙር ጨዋታዎች ላይ ያስመዘገበው ደካማ ውጤት ተከታዮቹ እንዲጠጉት አድርጓል፡፡ በተለይ መቀለ ከተማ የነጥብ ልዩነቱን ወደ 1 በማጥበብ አንደኛውን ዙር አጠናቋል፡፡

የደረጃ ሰንጠረዡን ስንመለከት ከዚህ ምድብ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማለፍ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ጥቂት ክለቦች ይመስላሉ፡፡ መሪው ወልዋሎ 32 ነጥብ ሲሰበስብ መቀለ ከተማ 31 ነጥቦች ይዞ አጠገቡ እየተነፈሰ ይገኛል፡፡ ባህርዳር ከተማ እና ሽረ እንዳስላሴ ደግሞ ተመሳሳይ 23 ነጥቦች ይዘው ከመሪው ወልዋሎ 9 ነጥቦች ርቀው ተቀምጠዋል፡፡ ከወልዋሎ እና መቐለ በታች የሚገኙ ክለቦችም በሁለተኛው ዙር ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማለፍ ተስፋቸውን የማለምለም ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል፡፡

የእርስ በእርስ ፍልሚያዎች

የምድቡ የመጀመርያ አራት ቡድኖች በሁለተኛው ዙር የሚያደርጓቸው የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ በሚያደርጉት ፉክክር ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የሜዳውን ጨዋታ አዲግራት ላይ ሲያደርግ የቆየው መቐለ ከተማም ወደ መቐለ መመለሱ በጉዞው ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛው ዙር

ከመቐለ ከተማ – ከሜዳው ውጪ

ከባህርዳር ከተማ – በሜዳው

ከሽረ እንዳስላሴ – ከሜዳው ውጪ

መቐለ ከተማ በሁለተኛው ዙር

ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ – በሜዳው

ከባህርዳር ከተማ – በሜዳው

ከሽረ እንዳስላሴ – ከሜዳው ውጪ

ባህርዳር ከተማ በሁለተኛው ዙር

ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ – ከሜዳው ውጪ

ከመቐለ ከተማ – ከሜዳው ውጪ

ከሽረ እንዳስላሴ – በሜዳው

ሽረ እንዳስላሴ በሁለተኛው ዙር

ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ – በሜዳው

ከመቐለ ከተማ – በሜዳው

ከባህርዳር ከተማ – ከሜዳው ውጪ

የመውረድ ስጋት

በዚህ ምድብ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ከሚደረገው ፉክክር ይልቅ ወደ አንደኛ ሊግ ላለመውረድ የሚደረገው ትግል ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ አምና ከከፍተኛ ሊጉ ወርዶ በዳሽን ቢራ እና ሙገር ሲሚንቶ መፍረስ ምክንያት በሊጉ የቆየው ሰሜንሸዋ ደብረብርሃን ዘንድሮ የሚተርፍ አይመስልም፡፡ በ10 ነጥቦች ግርጌ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከመውረድ ለመትረፍ 13ኛ ደረጃ ከሚገኘው ሱሉልታ ከተማ ጋር ያለውን የ7 ነጥቦች ልዩነት የማጥበብ ፈተና ይኖርበታል፡፡ 11 ነጥቦች የያዘው አራዳ ክፍለ ከተማም በመጣበት አመት ላለመውረድ ከባድ ፈተና የሚጠብቀው ሌለላው ክለብ ነው፡፡ አምና ጥሩ አጀማመር አድርጎ በመጨረሻ ለጥቂት ከመውረድ የተረፈው አዲስ አበባ ፖሊስም በወራጅ ቀጠናው የሚገኝ ሌላው ክለብ ነው፡፡

ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ጀምሮ የሚገኙ ክለቦች ከወራጅ ቀጠናው ያላቸው የነጥብ ርቀት ከ3 ያልበለጠ መሆኑን ስንመለከት የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ወደ ፕረምየር ሊግ ለማለፍ ከሚደረገው ፉክክር ይልቅ ወደ አንደኛ ሊግ ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር የሚጠነክር ይመስላል፡፡

አስተያየቶች

በምድብ ሀ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ የሚገኙ ክለቦች አሰልጣኞች በአንደኛው ዙር ጉዞ እና የሁለተኛ ዙር ተስፋ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ብርሀኔ ገብረእግዚአብሔር – የወልዋሎ አ.ዩ. አሰልጣኝ

ስለ ግማሽ ውድድር አመት

” እንደሚታወቀው የእኛ ምድብ በጣም ከባድ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ክለቦቹ ያሉበት ቦታ በጣም የተራራቀ በመሆኑ ረጅም ጉዞ እድናደርግ ተገደናል፡፡ በዚህ ምክንያት ውድድሩ ከባድ ሆኖብናል፡፡ ያም ሆኖ ግን የመጀመርያውን ዙር በመሪነት ማጠናቀቅ ችለናል።

የመጨረሻዎቹን አምስት ጨዋታዎች ላይ ያሳዩት ደካማ አቋም

ቅድም እንዳልኩት በረጃጅም ጉዞዎች መዳከማችን በአቋማችን ላይ መዋዠቅ አስከትሎበታል፡፡ ሌላው ትልቁ ችግር በዳኞች ላይ ያለው ችግር ነው ።

በሁለተኛው ዙር ወደ ቀደመው አቋም ስለመመለስ

ቡድናችን ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ያለበት ነው፡፡ ያም ሆኖ በአቅማችን የሚሆን ተጨዋቾች አምጥተን ወደ ራሳችን የቡድን አጨዋወት ለመቀየር አስበናል። 3ኛ ላይ ያለውን ቡድን በ 9 ነጥብ ነው የምንበልጠው፡፡ ያም ሆኖ ጠንክረን እንሰራለን፡፡ 8 ጨዋታዎችን በሜዳችን የምናደርግ በመሆኑ የበለጠ ዕድል አለን ብለን እናምናለን፡፡ ይህም ከምድቡ 1ኛ ወይም 2ኛ ሆነን እንደምናልፍ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡ ለዚህም ይረዳን ዘንድ ተጫዋቾችን እያሰፈረምን እንገኛለን።

ወደ ፕሪምየር ሊግ ጉዞ

እንደሚታወቀው ውጤት ሲመጣም ሆነ ሲጠፋ የሚወቀሰው አሰልጣኙ ነው፡፡ እኔ ደሞ ቡድኑን ከያዝኩት አንድ አመት ነው፡፡ ከያዝኩት ሰዓት ጀምሮ ቡድኑን በስነ ልቦና እንዲጠነክር እያደረኩኝ ነው፡፡ በተጫዋቾቹም ላይ የበለጠ  ተነሳሽ እዲሆኑ ስራ እየሰራን ነው፡፡ በተጨማሪም የልምምድ ገዜችንንም ከፍ አድርግን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ እየተንቀሳቀስን ነው።

ጌታቸው ዳዊት – የመቐለ ከተማ አሰልጣኝ

ስለ ግማሽ ውድድር አመት

” ለውድድሩ የነበረን ዝግጅት መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ውድድሩ ፈታኝ ነበር፡፡ ረጅም ጉዞ ይበዛው ስለነበር አስቸጋሪ ነበር ማለት ይቻላል።

ለሁለተኛው ዙር ቡድኑን ስለማጠናከር

በይበልጥ እየሰራን የምንገኘው ባሉን ተጨዋች ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ባሉን ክፍተቶች ላይ ተጨዋችን ለማምጣት እየሰራን ነው።

ጌታሁን ገብረጊዮርጊስ – ባህርዳር ከተማ

ዝግጅት ዘግይተን በመጀማራችን ትንሽ ተቸግረናል፡፡ እንዲሁም የምንፈልጋቸው ተጫዋቾች ውል ባለማለቁ የምንፈልገውን ያህል ክፍተቶችን ለመሙላት ተቸግረናል፡፡ እንደዛም ሆኖ ጥቅምት 15 ዝግጅት ጀምረን ሕዳር 23 ውድድሩን ጀምረናል፡፡ 8 እና 9 ጨዋታዎችን ያለሽንፈት መሄድ ችለን ነበር፡፡ ነገር ግን የስብስባችን ሰፊ አለመሆን ትልቅ ችግር ሆኖብናል፡፡ ቢሆንም ሁሉንም ተቋቁመን 3ኛ ሆነን አንደኛውን ዙር ጨርሰናል፡፡

ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን ነጥብ ለማጥበብ ያገኙትን ተደጋጋሚ ዕድል አለመጠቀም

በስብስብ እጥረት ምክንያት ተጫዋቾቹን በተደጋጋሚ በመጠቀማችን ይህ ሊከሰት ችሏል፡፡ ቡድኑን በከፍተኛ ውስጥ እንዴት መጨወት እንዳለባቸው አሰልጠናል፡፡ ይህ  በመሆኑም ነው ውጤቱን ማስጠበቅ የቻልነው፡፡ ከዚህ በላይ የዳኞች የውሳኔ ችግር በስፋት አጋጥሞናል፡፡ የእኛ አላማ ሁሌም የዳኝነት ሁኔታውን ፣ የተጋጣሚ ቡድን ደጋፊን እና ሜዳውን ጨምሮ አሽንፈን መውጣት ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ የዳኞቹ ውሳኔ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

በደጋፊዎቹ ላይ ያለውን መነቃቃት ስለመጠቀም

በመሰረቱ ይህን መነቃቃት የፈጠረው ውጤታችን ነው፡፡ ውድድሩን ስንጀምር ብዙ ደጋፊዎች በሜዳ ላይ  ያልነበሩ ሲሆን ነገር ግን ውጤቱ ሲመጣ የደጋፊዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ በዚህ ምክንያት በተጫዋቹች ላይ እና በቡድኑ ላይ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሮ የደጋፊን ጥቅም በከተማችን ላይም ከከተማችን ውጭ በደንብ አይተናል፡፡ አሁን ይህን ደጋፊ ለማርካትም ሆነ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ስኳዳችንን የማስፋት እና የተጋጣሚያችንን አጨዋወት በሚገባ አጥንቶ የማሸነፍ ስራ ላይ እንሰራለን፡፡

ለሁለተኛው ዙር ስለመጠናከር

በአጠቃላይ ተጨዋቾችን በአቅማችን ለማምጣት እየጣርን ነው፡፡ እስካሁን 5 ተጫዋቾችን ማምጣት ችለናል፡፡ ይህም የእኛን የስኳድ ጥበት ያስወግድልናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተጨዋቾቹ ጫና ሳይበዛባቸው መጨወት ይችላሉ ማለት ነው፡፡

ዳንኤል ጸሀዬ – ሽረ እንዳስላሴ

ስለ ግማሽ ውድድር አመት

አጭር ጊዜዬ ነው ቡድኑን ስቀላቀል፡፡ ቡድኑን ለማጠናከር እንዲሁም ቡድኑ ከአንደኛው ሊግ እንደማደጉ በደንብ መዋቀር ሰላለበት ትንሸ ጊዜ ፈጅቶብናል። ውድድሩ በጣም አድካሚ ነው፡፡ በተለይም የተጋጣሚ ሜደ አቀማመጥ፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ የራሱ የሆኑ ችግሮች አሉበት፡፡ የበጀት እጥረት እና የመሳሰሉትን ተቋቁመን እዚህ መድረሳችን በራሱ ትልቅ ድል ነው። በቡድኑ ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች በአብዛኛዎቹ ከከተማው የወጡ በመሆናቸው የሞራል ጥንካሬያችን ከፍተኛ ነው።

ስለ ሽረ ፈጣን እድገት

ቡድናችን በታሪኩ እንደዚህ ረጅም ጉዞ ተጉዞ አያውቅም፡፡ ውድድሩ በራሱ ከዚህ በፊት ከነበረው በይዘቱም ሆነ በፕሮግራም የተለየ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ከፍተኛው ሊግ በጣም ፈትኖናል፡፡ ቡድኑ ውስጥ  ያሉት ተጫዋቾች በሙሉ ጨዋታ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ካለን የስኳድ ጥበት አንጻር ውድድሩ ከባድ ነው፡፡ ቢሆንም ማኔጅመንቱ ፣ የአሰልጣኞች  ስታፍ ፣ በተለይም ደግሞ የተጨዋቾች ተነሳሽነት በጣም ትልቅ ነው።

ከመሪዎቹ ያላቸውን ልዩነት ስለማጥበብ

ዋናው አላማችን ፕሪምየር ሊጉ ማደግ ነው፡፡ የበጀት እጥረት ቢኖርብንም ቡድኑ ፕሪምየር ሊጉን እንዲቀላቀል የተሻለ ጥረት እናደርጋለን።

እንደ ኄኖክ ኢሳይያስ አይነት ተጫዎቾችን ማጣታቸው ያለው ተፅዕኖ

ኄኖክ ወደ ክለቡ ሲመጣም የተሻለ ደሞዝ አግኝቶ ሳይሆን ከኔ ጋር ባለው ጥሩ ግንኙነት ምክንያት ነው፡፡ እሱን መተካት ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ቡድኑን ስሰራው እንደቡድን እንዲጫወት ስላደረኩት እንቋቋማለን፡፡

በሁለተኛ ዙር ክለቡን ስለማጠናከር

የክለቡ የስራ አመራር ጥሩ የሚባል መነሳሳት ይታይባቸዋል፡፡ እኔም በምችለው መጠን ቡድኑን ወደ ስኬት እንድወስደው የተቻላቸውን እገዛ እያደረጉልኝ ነው፡፡

Leave a Reply