የጨዋታ ሪፖርት| የአማራ ደርቢ በአፄዎቹ የበላይነት ተጠናቋል

20ኛው ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዛሬው እለት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የአማራ ደርቢን አስተናግዶ በሜዳው አንድ ጨዋታ እንዳያካሄድ ቅጣት የተጣለበት ፋሲል ከተማ ወልዲያ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል አድራጊነቱ ተመልሷል፡፡

ፋሲል ከተማዎች በሚታወቁበት የ4-3-3 ቅርፅ ከሶስት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ቡና በሜዳው የተሸነፈውን ቡድን ይዘው ሲጀምሩ ወልዲያ ከተማዎች በ19ኛው ሳምንት በሜዳው መከላከያን ካሸነፈው ቡድን ታዬ አስማረን በዳንኤል ብቻ ተክተው ወደ ጨዋታ ገብተዋል፡፡

በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ፋሲል ከተማዎች በፈጣን የመስመር አጨዋወት በተደጋጋሚ ወደ ወልዲያ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በተለይም በ6ተኛው ደቂቃ የፋሲሎች የግራ መስመር አጥቂ የሆነው አቡደረህማን ሙባረክ ፍጥነቱን ተጠቅሞ አፈትልኮ ወደ ወልዲያ የግብ ክልል ከደረሰ በኃላ ያሻማውን ኳስ ኤዶም ሆሮሶውቪ ገጭቶ ቢሞክርም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ለትማ ወጥታለች፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ኃላ አፈግፍገው በሚገኙ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማስቆጠር አቅደው የገቡ የሚመስሉት ወልዲያዎች በጥልቀት ተስበው ከተከላከሉ በኃወደፊት ለማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግር በጣም የዘገየ ከመሆኑ የተነሳ በተለያዩ አጋጣሚዎች በጨዋታው በወልዲያ በኩል ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው የመስመር አማካዩ ያሬድ ሀሰን በተደጋጋሚ በማጥቃት ወረዳው ላይ የሚያግዘው ተጫዋች እጦት ብቻውን ሲደክም ተስተውሏል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በስፋት እንደተስተዋለው እንደ አብዛኛዎቹ የሊጉ ተሳታፊ ቡድኖች ፋሲል ከተማ በሚያጠቃበት ወቅት ወደ ሁለት ቡድንነት ሲከፈል በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በበርካታ አጋጣሚዎች ተስተውሏል፡፡ በዚህ ጊዜ በተከላካይ መስመሩ እና በአማካዮቹ መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት ለመጠቀም ከመሞከር ይልቅ በበርካታ አጋጣሚዎች ወልዲያዎች በቀጥተኛ አጨዋወት በተለይም ከተከላይ ክፍላቸው እና ከግብ ጠባቂያቸው በቀጥታ በሚጣሉ ኳሶች መጫወትን ምርጫቸው አድርገው ታይተዋል፡፡

ወልዲያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለት አጋጣሚዎች በግራ መስመር በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ያሬድ ሀሰን በግሩም ሆኔታ ወደ መሀል ያሻማቸውን ኳሶች ኤሪክ ኮልማንና ሀብታሙ ሸዋለም በሚያስቆጭ ሁኔታ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ፋሲል ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት የግራ መስመር ተከላካዩ ሰኢድ ሁሴን አሻምቶ ኳስ ይስሃቅ መኩሪያ የወልዲያ ተጫዋቾች ስህተት ታግዞ ቡድኑን መሪ ያደረገችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ከግቧ መቆጠር በኃላ በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ፋሲል ከተማዎች ያገኙትን የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ኤርሚያስ ሀይሉ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

የወልዲያው አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ኤሪክ ኮልማንን በጫላ ድሪባ እንዲሁም ሀብታሙ ሸዋለምን አስወጥተው በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ በመተካት ፊት ላይ የአጥቂ ቁጥራቸውን ወደ ሶስት በማሳደግ የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ በአንጻሩ በፋሲል ከተማዎች በኩል ከሌሎቹ የሊጉ ቡድኖች በተለየ መልኩ ከኳስ ከተነጠቁ በኃላ በፍጥነት ኳሱን መልሰው ለመንጠቅ የሚያደርጉት ጥረት በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

የሀይል አጨዋወት በስፋት በተስተዋለበት በዚሁ ጨዋታ በወልዲያ በኩል አዳሙ መሀመድ እንዲሁም በፋሲል በኩል ሰለሞን ገብረመድህንና አብዱረህማን ሙባረክ በጉዳት ከሜዳ ተቀይረው ለመውጣት ተገደዋል፡፡
በጨዋታው ላይ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች በሜዳው ተገኝተው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ተስተውሏል፡፡ በተይም በካታንጋ አካባቢ በብዛት ተቀምጠው የነበሩት የአፄዎቹ ደጋፊዎች የድጋፍ ድባብ ልዩ ነበር፡፡

በዚህ ውጤት መሠረት ፋሲል ከተማዎች በሁለተኛው ዙር ከተከታታይ ሶስት ሽንፈቶች በኃላ ባስመዘገበው የመጀመሪያ ድል በ29 ነጥብ አሁንም በ6ኛ ደረጃ መቀመጥ ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *