የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዳሰሳ – ምድብ ለ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አንደኛ ዙር ተገባዶ ክለቦች ሁለተኛውን ዙር ለመጀመር እየተሰናዱ ይገኛሉ፡፡ በሁለት ምድብ ተከፍሎ እየተደረገ የሚገኘው ውድድር ሁለተኛ ዙር በመጪው ሳምንት የሚጀመር ሲሆን የምድብ አንድን የአንደኛ ዙር እንቅስቃሴ ፣ የሁለተኛ ዙር ጉዞ እና የአሰልጣኞችን አስተያየት አካተን ያሰናዳነውን ፅሁፍ በትላንትናው እለት ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ የምድብ ሁለትን ይዘን ቀርበናል፡፡

ለሀሉም ክፍት የሆነው ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ተስፋ

የምድብ ለ የመጀመርያ ዙር ሲጠናቀቅ ሁሉም ክለቦች ለማለት በሚያስችል መልኩ በነጥብ ተጠጋግተው አጠናቀዋል፡፡ ከ1ኛ እሰከ 10ኛ ያሉት ክለቦች ወደ ፕሪምየር ሊግ የማደግ ተስፋ ያላቸው ሲሆን የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ይዘው የሚገኙ ክለቦችም የማደግ እድላቸው አልተሟጠጠም፡፡

ምድቡን ጅማ ከተማ በ26 ነጥብ ሲመራ ሀላባ ከተማ በ24 ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና በ23 ይከተላሉ፡፡ 10ኛ ላይ የሚገኘው ፌዴራል ፖሊስ ከመሪው የራቀው በ6 ነጥቦች ብቻ መሆኑ አስገራሚ ነው፡፡ የመጨረሻ ደረጃ የያዘው ነቀምት ከተማ ከጅማ ከተማ በ14 ደረጃዎች ቢያንስም የራቀው በ11 ነጥቦች ብቻ ነው፡፡ በምድብ ሀ መሪው ወልዋሎ 3ኛ ደረጃ ከሚገኘው ባህርዳር ከተማ በ9 ነጥቦች መራቁን ስንመለከት የምድብ ለ የሁለተኛ ዙር ጉዞ ይበልጥ አጓጊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በዚህ ምድብ የሚገኙት ክለቦች ተቀራራቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸው በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ይዞ ለመውጣት አዳጋች አድርጎታል፡፡ መሪው ጅማ ከተማ የሰበሰበውን 26 ነጥብ ስንመለከትም መሰብሰብ ከነበረበት 57% ብቻ ሰብስቦ ከአናት መቀመጡ የምድቡ ጠንካራነት የሚያሳይ ነው፡፡

የእርስ በእርስ ግንኙነቶች
በሁለተኛው ዙር የተሻለ ወጥነት ማሳየት የሚችል ቡድን ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማደግ ህልሙን ማሳካት ይችላል፡፡ በተለይም እየያንዳንዱ ጨዋታ ካለው ዋጋ እና በከፍተኛ ሊጉ ከሜደ ውጪ ለማሸነፍ አስቸጋሪ ከመሆኑ አንጻር ክለቦች ከጠንካራ ቡድኖች በሜዳቸው የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ለጉዟቸው ማማር ወሳኝነታቸው የጎላ ነው፡፡ በአንጻሩ ከሜዳ ውጪ ተጉዞ የሚያሸንፍ ቡድንም ልዩነት የመፍጠር አቅምን ያገኛል፡፡

የምድቡ መሪ ጅማ ከተማ በዚህ ረገድ እድለኛ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ከተከታዮቹ ቡድኖች ጋር የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በሜዳው ማደድረጉ ተጠቃሚ ያደርገዋል፡፡

የሁለተኛ ዙር ወሳኝ ጨዋታዎች (ከ1-4 ደረጃ የሚገኙ ቡድኖች)

ጅማ ከተማ

ከሀላባ ከተማ – በሜዳው (ግንቦት 5)

ከወልቂጤ ከተማ – በሜዳው (ሰኔ 18)

ከሀዲያ ሆሳዕና – በሜዳው (ሚያዝያ 23)

ሀላባ ከተማ

ከጅማ ከተማ – ከሜዳው ውጪ (ግንቦት 5)

ከወልቂጤ ከተማ – በሜዳው (ሚያዝያ 28)

ከሀዲያ ሆሳዕና – ከሜዳው ውጪ (ሰኔ 18)

ወልቂጤ ከተማ

ከጅማ ከተማ – ከሜዳው ውጪ (ሰኔ 18)

ከሀላባ ከተማ – ከሜዳው ውጪ (ሚያዝያ 28)

ከሀዲያ ሆሳዕና – ከሜዳው ውጪ (ሚያዝያ 17)

ሀዲያ ሆሳዕና

ከጅማ ከተማ – ከሜዳው ውጪ (ሚያዝያ 23)

ከሀላባ ከተማ – በሜዳው (ሰኔ 18)

ከወልቂጤ ከተማ – በሜዳው (ሚያዝያ 17)

ላለመውረድ የሚደረግ ትንቅንቅ

ከዚህ ምድብ አንደኛ ዙር  ወደ ፕሪምየር ሊግ እንደሚያልፉት ሁሉ ወደ አንደኛ ሊግ የሚወርዱት 3 ቡድኖችን ፍንጭ አላሳየንም፡፡ በሁለተኛው ዙር አቋሙ የሚዋዥቅ ማንኛውም ቡድን ሊወርድ ይችላል፡፡ በተለይም ከደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ጀምሮ የሚገኙ ክለቦች የመውረድ ስጋት ያንዣበበባቸው ናቸው፡፡

አስተያየቶች

አቶ ናስር የጅማ ከተማ ቡድን መሪ

(ጅማ ከተማ ከአሰልጣኝ ክፍለሌ ቦለልተና ጋር በመለያየቱ የቡድን መሪውን አስተያየት ለማካተት ተገደናል)

ግማሽ ውድድር አመት

ወድድሩ ጥሩ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የግማሽ አመቱን ውድድር በሜዳችን እና ከሜዳችን ውጭ ያደረግናቸው ጨዋታዎች በሚል መክፈል እንችላለን፡፡ በሜዳችን ካደረግናቸው ጨዎታዎች ከሞላ ገደል ነጥብ መሰብሰብ ችለናል፡፡ ነገር ግን ከሜዳችን ውጭ ያሉትን ጨዋታዎች ነጥብ እየጣልን መጥተናል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የተጋጣሚ ቡድን የሜዳ አቀማመጥ ጥሩ አለመሆኑ እና የተጨዋቾች ጉዳት ነበር።

በቀጣይ ዙር መሪነቱን አስጠብቆ ስለመቀጠል

እንደሚታወቀው ጅማ አንደኛ ሆኖ የመጀመርያውን ዙር እንዲጨርስ ከረዳው ዋንኛው ነገር የህዝቡ እና የአስተዳደሩ ድጋፍ ሲሆን ሌላው ተጨዋቾች ባሳዩት ትጋት ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቡድኑን አሰልጣኝ የቀየርን ሲሆን አሰልጣኝ መኮንን አምተጥተናል፡፡ ሌላው አጠንክረን እየሰራን የምንገኘው በተጨዋቹች የሜዳ ላይ ዲስፒሊን ነው።

ክለቡን ይበልጥ ለማጠናከር የተወሰዱ እርምጃዎች

ቡድኑን ለማጠናከር የተጫዋቾች ዝውውር ላይ እየሰራን እንገኛለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተጫዋቾች ከሜዳ ውጭ ያላቸውን ባህሪ በማሻሻል ላይ በስፋት እየሰራን እንገኛለን።

አላምረው – የሀላባ ከተማ አሰልጣኝ

ግማሽ ውድድር አመት

ወድድሩ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ምድቡም በጣም ፈተኝ ነበር፡፡ በትኩረት ችግር ነጥቦች ብንጥልም ይህ በሁለተኛው ዙር የሚደገም አይሆንም፡፡ ዘንድሮ ከመጀመሪያ ጀምሮ የህዝቡ ድግፍ ልዩ ነው፡፡ ይህም በጣም ጥሩ መነቃቃት በቡድኑ ላይም በአስተዳደሩ ላይ ፈጥሯል፡፡ እስካዘሬ ጫፍ ደርስን ነበር የምንቀረው፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ ቀሪዎቹን 8 ጨዎታዎች በሜዳችን እንደማድረጋችን በጥሩ ነጥብ አንደኛ ሆነን እንጨርሳለን።

በሁለተኛ ዙር

በክፍተታችን ላይ በደንብ እየሰራን እንገኛለን፡፡ ተጨዋቾቹ በቂ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ ክለቡም ከተለያዩ ክለቦች ተጨዋቾች ለማምጣት እየሰራ ነው፡፡

አዲሱ ካሳ – የወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ

ግማሽ ውድድር አመት

አንደኛው ዙር ጥሩ ነበር፡፡ የኛ ቡድን አጀማመር ላይ እንደጠበቅነው ጥሩ አልነበረም ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ መሀል ራሳችንን አስተካክለን ጥሩ ብንሆንም መልሰን ነጥብ መጣል ተስተውሏል፡፡ ወደመጨረሻቹ ጨዋታዎች ላይ ደግሞ ጥሩ ሆነናል፡፡

ከብሔራዊ ሊግ አድጎ ተፎካካሪ መሆን

ከፍተኛ ሊጉ ቢከድም እኛ ጥሩ ነገር እያሳየን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት ሙሉ ለሙሉ ተሟልተናል ማለት አይቻልም፡፡ የከፍተኛው ሊግ በቁጥር ከብሔራዊ ሊግ ከፍ ይላል፡፡ በዚህም ላይ ፈታኝ ነው፡፡ ይህን ነገር ለመለወጥ በተጫዋቾቹ ላይ በደንብ እየሰራን ነው ።

የዲስፕሊን ክፍተቶች

ዲስፕሊን ላይ እየታየ ያለው ነገር ከአምና እና ካቻምናው የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን የለም ማለት አልችልም፡፡  ሁለት ጨዋታዎች ላይ ይህ ነገር ታይቷል፡፡ ለዚህም እኛ ይህን የቤት ስራ ወስደን እየሰራን በተቻለን ነገር ሜደ ላይ በጨዋታ  መጨረስ ነው ያለብን፡፡

ለሁለተኛ ዙር ክለቡን ስለማጠናከር

በአንደኛው ዙር በቂ ግቦች አላስቆጠርንም፡፡ በግማሽ አመት 17 ጎል ብቻ ነው ያስቆጠርነው፡፡ ይህን ተረድተን የአጥቂ መስመሩን እያጠናከርን እንገኛለን፡፡

ጳውሎስ ጌታቸው – የሀዲያ ሆሳዕና አሰልጣኝ

ግማሽ ውድድር አመት

ውደድሩ ጥሩ የነበረ ሲሆን ከፍተኛ የነጥብ መጠጋጋትም ይታይበታል፡፡ በአጠቃላይ ክለቦቹ ጥሩ ፉክክር አድርገዋል፡፡ ቡድኑን ስረከበው ሙሉ አልነበርም፡፡ ይህም ትንሽ ተፅዕኖ ቢያስድርም ጠንከረን እየሰራን ጥሩ በሆነ የኳስ እንቅስቃሴ እዚህ ደርሰናል፡፡ በሁለተኛው ዙር በደንብ አጠናክረን ነጥብ በደንብ እንሰበስባለን ፤ በአደኝነትም እንጨርሳለን፡፡ እዚህ ላይ የምናስተውለው ከፍተኛው ሊግ ምን ያህል ከባድ እና ፈተኝ እንድሆነ ነው፡፡ ይህም ለአገራችን እግርኳስ ጥሩ ግብአት መሆን እንደሚችል ነው የሚያሳየን፡፡ በአጠቃላይ ከከፍተኛ ሊግ ለሚያደገው ቡድን ፕሪምየር ሊጉ አይከብደውም ማለት ነው።

በሁለተኛ ዙር ክለቡን ስለማጠናከር

ቡድኑን ለማጠናከርና ተፎካካሪ ለመሆን ዝውውር ጀመርናል፡፡ ተጫዋቾችም እያስፈረምን እንገኛለን፡፡

Leave a Reply