የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ተጠባቂውን ጨዋታ በአዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል አስተግዶ በባለሜዳው የበላይነት ተጠናቋል፡፡
ጨዋታው ልዩ የሆነ የደጋፊ ድባብ የታየበት ፣ ጥንቃቄ የታከለበት እንቅስቃሴ የተተገበረበት ፣ የተጨዋች ቅያሪ ልዩነት የፈጠረበት ፣ አዳማ ከተማ ተሽሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተዳክሞ የታየበት የጨዋታ እንቅስቃሴ አሳይቶናል፡፡
ጨዋታው በሳላዲን አማካኝነት ከተጀመረበት ደቂቃ አንስቶ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ ብልጫ የወሰዱት ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ሲሆኑ በ10ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ከግራ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ ፍሬው ጌታሁን እንደምንም ያወጣበት ሙከራ የአዳማ ከተማ የመጀመርያው አስደንጋጭ ሙከራ ነበር።
ከዚህ በኋላ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ በአዳማ በኩል በግራ መስመር ይጫወቱ የነበሩት ሱራፌል ጌታቸው እና ሱሌማን መሀመድ በተደጋጋሚ የቅዱስ ጊዮርጊስን የተከላካይ ስፍራ ቢረብሹም ወደ ጎል የሚጥሏቸው ኳሶች አጥቂዎቹ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ፈረሰኞቹ በአንፃሩ ተዳክመው በቀረቡበት የመጀመርያው አጋማሽ 32ኛው ደቂቃ አበባው ቡጣቆ ያሻማውን ቅጣት ምት ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ ገጭቶ ጃኮ ፔንዜ ያዳነበት ለፈረሰኞቹ ብቸኛ የመጀመርያም የመጨረሻም ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
ጨዋታው ግለቱን ጠብቆ በፈጣን እንቅስቃሴ ቀጥሎ ባለበት ሁኔታ በተደጋጋሚ በሁለቱም በኩል በሚሰሩ ጥፋቶች ጨዋታው እየተቆራረጠ ቀጥሎ የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡
ከእረፍት መልስ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ቡድኖቹ የሚፈልጉትን የጨዋታ አቀራረብ ለመተግበር ቢቸገሩም እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ አዳማ ብልጫ ነበረው። ያም ቢሆን ሁለቱም ቡድኖች ከሚከተሉት የጨዋታ ዘይቤ እና ከነበራቸው ጠንካራ የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾች አኳያ የተቀዛቀዘ እና የግብ እድል ያልተፈጠረበት ሆነኖ ዘልቋል፡፡
በ81ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ጆርጅን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው እና የዕለቱ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ዳዋ ሆቴሳ ከቀኝ መስመር ሱራፌል ዳኛቸው ያሻማውን ቅጣት ምት በግንባሩ በመግጨት የቀድሞ ክለቡ ላይ ግሩም ግብ አስቆጥሯል፡፡
ከጎሉ መቆጠር በኋላ አዳማዎች ተጨማሪ ጎል ሊሆን የሚችል ኳስ አግኝተው ዳዋ ሆቴሳ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ የጎል ልዩነቱን ማስፋት በቻሉ ነበር። ፈረሰኞቹም አቻ ለመሆን የሚያደርጉት ጥረት እምብዛም ሳይታይ ጨዋታው በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች ወደር የሌለው ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውሏል። በርካታ የሆኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችንም በወድማማችነት መንፈስ በክብር ተቀብለው በክብር ሸኝተዋል፡፡ ቁጥራቸው ከ150 በላይ የሚሆኑ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች እና የኮሚኒቲ ፖሊስ አባላት በስታድየሙ ውስጥ ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር የሰሩት ተግባር እጅግ ሊያስመሰግናቸው ይገባል።
ውጤቱን ተከትሎ አዳማዎች 34 ነጥብ በመሰብሰብ ደረጃቸውን በማሻሻል ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ሲችሉ ከራቁበት የዋንጫ ፉክክርም መመለስ ችለዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈቱን ቢያስተናግድም አሁንም የሊጉ መሪ ከመሆን አላገደውም፡፡