የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ በ3 ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው መከላከያ 3-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። ጨዋታው በሊጉ ሁለተኛ ዙር ጥሩ እንቅስቃሴ እያሳየ ባለው ሀዋሳ ከተማ እና ከሳምንት በፊት የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሸነፍ በቻለው መከላከያ መሀል የተደረገ እንደመሆኑ ተጠባቂ የነበረ ቢሆንም የታሰበውን ያህል ፉክክር ሳይታይበት በሀዋሳ የበላይነት ተጠናቋል።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለረጅም ጊዜ ላገለገሉት እና በዚህ ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት አቶ ዘውዱ ካሳሁን የህሊና ፀሎት ተደርጓል።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ጠቂት ደቂቃዎች ነበር የወሰደባቸው። በሁለተኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ በቀኝ መስመር በኩል ተከላካዮችን በማለፍ ወደ አደጋ ክልሉ የላከውን ኳስ ጃኮ አረፋት በማስቆጠር ሀዋሳ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ተጭነው መጫወት የቀጠሉት ሀዋሳ ከተማዎች በ22ኛው ደቂቃ ልዩነቱን ያሰፉበትን ግብ አስቆጥረዋል። ፍሬው ሰለሞን በግራ በኩል ያሻገረውን ኳስ የመከላከያው ተከላካይ አወል አብደላ ገጭቶ ሲመልሰው በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ጋዲሳ መብራቴ አግኝቶ በግሩም ሁኔታ ወደግብ ቀይሮታል።
ከአንድ ደቂቃ በኋላ የሀዋሳ ከተማው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳ ሜዳው አንሸራቶት ሲወድቅ ኳሱን ሚካኤል ደስታ አግኝቶ ወደ ፊት ልኮት ምንይሉ ወንድሙ ቢያስቆጠረውም ከጨዋታ ውጪ ነው ተብሎ መሻሩ የመከላከያ ተጫዋቾችን እና አሰልጣኞች በኩል ቅሬታ የፈጠረ ነበር።
ሀዋሳዎች የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠር የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ፍሬው ሰለሞን በ37ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ ወደግብ መትቶ ወደውጪ የወጣበት ኳስ የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች ላይ ጃኮ አረፋት በመከላከያ ተከላካዮች ስህተት ያገኘውን ኳስ ለጋዲሳ መብራቴ አሾልኮለት ጋዲሳም በጥሩ አጨራረስ የሀዋሳን ሶስተኛ ግብ አስቆጥሮ ክለቡ 3ለ0 እየመራ ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመራ አስችሏል። በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ መከላከያዎች ልዩነቱን ለማጥበብ ባዬ ገዛኸኝን ቀይረው ወደ ሜዳ በማስገባት አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ግልፅ የግብ አጋጣሚዎችን ግን መፍጠር አልቻሉም ነበር። በ62ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ በቅጣት ምት ወደግብ ከሞከረው እና በ90ኛው ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ ከጠባብ አንግል መትቶ ከሳተው ኳስ ውጪ በመከላከያ በኩል ይህ ነው የሚባል ሙከራ አልተደረገም።
ለጨዋታው መጠናቀቂያ 4 ደቂቃ ሲቀረው የመከላከያው ምንተስኖት ከበደ በአስጨናቂ ሉቃስ ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ደረጃውን በማሻሻል በ24 ነጥብ ወደ 8ኛ ከፍ ማለት የቻለ ሲሆን ተሸናፊው መከላከያ በተመሳሳይ 24 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።