የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 0-3 ሀዋሳ ከተማ

ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ
ከጨዋታው መጀመሪያ አንስቶ ተጠንቅቀን ነው የቀረብነው፤ የዚህ ምክኒያትም ምንም እንኳን ባለፉት ጨዋታዎች ጥሩ ብንሆንም በመጨረሻው ጨዋታ በደደቢት በሜዳችን የደረሰብን ያልታሰበ ሽንፈት ተከትሎ ቡድኑ ላይ ትንሽ አለመረጋጋት ስለነበረ ነው – በራስ መተማመናቸውም በተወሰነ መልኩ ወርዶ ነበረ። መከላከያ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ ነው የመጣ በመሆኑ ተጠንቅቀን ለመጫወት ነው የሞከርነው።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግብ ማስቆጠራችን የጠቀመን ይመስለኛል። ከዚያ በኋላ የነበረው ጨዋታ ከባድ አልነበረም። መከላከያ ጠንካራ ቡድን ነው፤ ግን እኛ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀሙ ላይ የተሻልን ስለነበርን በቀላሉ አሸንፈን ወጥተናል። 

ግቦች ካስቆጠርን በኋላ እነርሱ ግብ ለማግኘት ሲሞክሩ የተጫወቱበት መንገድ ለኛ  ጨዋታውን በእርግጥ ቀላል አድርጎልናል። በብዛት ተሻጋሪ ኳሶችን ነበር የሚሄዱት፤ እነዚያን ለመቆጣጠር አልተቸገርንም ነበር። የእኛ ጥሩ መሆን እና አጋጣሚዎችን መጠቀም ግን ለነርሱ ጨዋታውን አክብዶባቸው ነበር።

ሊጉ ዘንድሮ በጣም አስቸጋሪ ነው። እኛ በመጀመሪያው ዙር ብዙ ነጥቦችን ጥለን ነበር። ዘግይተን ነው ነጥብ መሰብሰብ የጀመርነው። ብዙ ወጣት ተጫዋቾችን ይዘን ነው እየታገልን ያለነው። በቀጣይ ከፋሲል ከተማ ጋር ያለንን ጨዋታ ጨምሮ ከፊታችን ያሉትን ጨዋታዎች የግድ ማሸነፍ ይጠበቅብናል። በሊጉ መቆየት የምንችለው ይህንን ካደረግን ብቻ ነው።

​በለጠ ገብረኪዳን- መከላከያ
ከእረፍት በፊት እንዳያችሁት የእኛም ስህተት ተጨምሮበት ተጋጣሚያችን የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ የነበረን የጥንቃቄ ጉድለት ግቦች እንዲቆጠሩብን አድርጓል። ጨዋታው ያለቀው በመጀመሪያው አጋማሽ ነው ማለት ይቻላል፤ በ45 ደቂቃዎች ነው ተሸንፈን የወጣነው።። ለቀጣይ ጨዋታዎቻችን ትልቅ ትምህርት ይሆነናል።

ትልቅ መሰረታዊ ችግር አልነበረብንም፤ የትኩረት ማነስ ነው የነበረው። በተለይ በተከላካይ ክፍላችን ላይ ከመጀመሪያው ጀምሮ ተጠንቅቆ ያለመጫወት ችግር ነበር።

ያለፈውን ጨዋታ አሸንፈን መምጣታችን የተሻለ ነገር እንሰራለን ብለን እንድንመጣ አድርጎን ነበር፤ በሞራልም ጥሩ ነበርን። ሆኖም ግን በእግርኳስ አንዳንዴ እንደዚህ አይነት ነገር ያጋጥማል።

ቡድናችን በዚህ ዓመት ወደ ግብ መድረስ ቢችልም የአጨራረስ ችግር ግን አለብን። አሁን እነ ባዬ ገዛኸኝ ከጉዳታቸው እየተመለሱ ስለሆነ በተወሰነ መልኩ ተሻሽለን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ።

Leave a Reply