የጨዋታ ሪፖርት | አርባምንጭ ከተማ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት መርሀ ግብር አርባምንጭ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ 2-0 በማሸነፍ የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ 3 ነጥቡን አስመዝግቧል፡፡

በጨዋታው በሙሉ ደቂቃዎች ጫና ውስጥ የነበረው አርባምንጭ ከተማ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎችን በጥንቃቄ ሲጫወት እንግዳው ኤሌክትሪክ በአንፃሩ ለማጥቃት ሲሞክሩ ታይቷል፡፡ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ፀጋዬ አበራ በ15ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂው ሱሌይማን አቡ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስም የመጀመርያ ሙከራ ነበር፡፡

ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር አርባምንጮች ጫና እየፈጠሩ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን አማኑኤል ጎበና በጨዋታውን ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ድንቅ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ በኤሌክትሪኮች በኩል እምብዛም የግብ እድል መፍጠር ያልቻሉ ሲሆን በ23ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ የሰጠውን ግሩም ኳስ አጥቂው ፍፁም ገብረማርያም ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀም ቀርቷል፡፡

ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ሲሰነዝሩ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች በ40ኛው ደቂቃ ተሳክቶላቸው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል፡፡ በማጥቃቱ ረገድ የተዋጣ እንቅስቃሴ ያሳየው ፀጋዬ አበራ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አምበሉ አማኑኤል ጎበና አስቆጥሮ አርባምንጭን መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ አምርተዋል::

ኤሌክትሪኮች ግብ የሚሆን እድል በመፍጠር ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን ሙሉአለም ጥላሁን ከፍፁም ገ/ማርያም ያገኛት ኳስ አቻ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ ብትሆንም ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡

በአርባምንጭ በኩል የተሻለ ሲንቀሳቀስ የነበረው አጥቂው ፀጋዬ አበራ ጉዳት አጋጥምት ለህክምና ከሜዳ በመውጣቱ ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር፡፡ ሆኖም ጭንቅላቱ ታሽጎለት ዳግም ወደ ሜዳ የተመለሰው ፀጋዬ አበራ ታደለ መንገሻ በግል ጥረቱ ያቀበለውን ኳስ በ59ኛው ደቂቃ አስቆጥሮ የአርባምንጭን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡ ፀጋዬ ኋላ ላይ ጉዳቱ አገርሽቶበት በ76ኛው ደቂቃ በአፋጣኝ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል፡፡

ኤሌክትሪኮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተደጋጋሚ ጥረቶች አድርገዋል፡፡ በተለይም የመስመር ተከላካዩ አወት ገብረሚካኤል የሚያሻግራቸውን ኳሶች አጥቂዎቹ ፍፁም እና ሙሉአለም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተው ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ውጤቱ በተከታታይ ጨዋታዎች ውጤት ርቋቸው ለቆዩት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጸጋዬ እፎይታን ሲሰጥ በሁለተኛው ዙር ተሻሽሎ የቀረበው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል፡፡

Leave a Reply