በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ ወደ አዳማ ከተማ ያመራው ዳዋ ሁቴሳ የአዳማ ከተማን የውድድር ዘመን ጉዞ በሚወስነው ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ አስቆጥሮ ክለቡን ወደ ዋንጫው ፉክክር መልሶታል፡፡ ዳዋ ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት የማሸነፍያዋን ግብ በማስቆጠሩ መደሰቱን ተናግሯል፡፡
ተቀይሬ ስገባ አንድ ነገር ሰርቼ እንደምወጣ አስቤ ነበር የገባሁት፡፡ አሰልጣኞቼም ሲያስገቡኝ በእኔ ሙሉ እምነት ነበራቸው፡፡ እኔም ተቀይሬ ገብቼ ጥሩ ተንቀሳቅሻለው፡፡ በእኔ ግብ 3 ነጥብ በማሳካታችን በጣም ተደስቻለው፡፡ ” ብሏል፡፡ ዳዋ አያይዞም የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ አስቆጥሮ ደስታውን የገለጸበትን መንገድ አብራርቷል፡፡
” በጣም የተለየ ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቀድሞ ክለቤ ነው፡፡ ጥሩ ጊዜ አላሳለፍኩም ፤ ያ ግን የአቅም ችግር ሳይሆን የተለያዩ ችግሮች ነበሩ፡፡ ያም ቢሆን አዳማ መጥቼ ጥሩ ጊዜ እያሳለፍኩ ነው። ይህ ጨዋታ አቅሜን የማሳይበት አጋጣሚ ነበር፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም አቅሜን አሳይቼ የቀድሞ ክለቤ ላይ ጎል በማስቆጠሬ ደስተኛ ነኝ፡፡ ”
አዳማ ከተማ ከጥሩ አጀማመር በኋላ መንሸራተት አሳይቶ ከመሪዎቹ በነጥብ ርቆ ነበር፡፡ በቅርብ ጨዋታዎች ባሳየው አቋም ደግሞ ወደ መሪዎቹ ፉክክር መመለስ ችሏል፡፡ ዳዋ ሁቴሳም ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገኙት ሶስት ነጥብ ወሳኝ እንደሆነ ገልጿል፡፡
” ዛሬ በጣም ወሳኝ ሦስት ነጥብ አግኝተናል፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉት ቀሪ ጨዋታዎች ያለንን አሸናፊነት አስጠብቀን በመዝለቅ ወደ ዋንጫ አሸናፊነት የምናደርገው ጉዞ ማሳመር እንፈልጋለን።”