የጨዋታ ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት የሊጉን አናት ተቆናጧል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 3-1 በማሸነፍ የሊጉን መሪነት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተረክቧል፡፡

ከተያዘለት ሰአት 15 አምስት ደቂቃዎች ዘግይቶ በተጀመረው ጨዋታ ባለሜዳው ሲዳማ ቡና ከጅማሮው አንስቶ በተጋጣሚው ላይ ብልጫ ወስዶ ሲጫወት ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በተለይ በመጀመሪወቹ 15 ደቂቃዎች በተጋጣሚው ሲዳማ ቡና የጨዋታ ብልጫ ተወስዶበታል፡፡

ሲዳማ ቡና ቀዳሚ የሆነበትን ግብ ለማግኘት የፈጀበት ሁለት ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ ላኪም ሳኒ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን የሰራውን ስሆተት ተጠቅሞ በጥሩ ሁኔታ ያመቻቸለትን ኳስ ትርታዬ ደመቀ አስቆጥሮ ሲዳማን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላም ላኪ ሳኒ የግብ ልዩነቱን ሊያሰፋበት የሚችለውን እድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

በ27ኛው ደቂቃ እያሱ ታምሩ ወደ ሲዳማ የአደጋ ክልል በረጅሙ የላካት ኳስ አቡዱልከሪም መሀመድ ተቆጣጥሮ ኢትዮጵያ ቡናን አቻ አደረገ ሲባል አንተነህ ተስፋዬ በአስደናቂ ሁኔታ የነጠቀው ኳስ ቡናዎች የፈጠሩት የመጀመርያ የግብ እድል ነበር፡፡ ቡናዎች ከመጀመሪያው አስራአምስት ደቂቃዎች ከፈጠሩት መዘናጋት ተላቀው አልፎ አልፎ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል ደርሰዋል፡፡ በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቡና የተሰለፈው ታዳጊው አቡበከር ነስሩ የሚያደርገው አመርቂ እንቅስቃሴ በቡና በኩል የሚጠቀስ ነበር፡፡

በ34ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ኤልያስ ማሞ ከአበበ ጥላሁን ጋር ተጋጭቶ በደረሰበት ጉዳት ወደ ህክምና በአንቡላንስ ያመራ ሲሆን አክሊሉ ዋለልኝ ተክቶት ገብቷል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ታይተዋል፡፡ ሲዳማዎች እጅግ ለግብ የቀረቡ እድሎችን በላኪ ሰኒ እና አዲስ ግደይ አማካይነት መፍጠር ቢችሉም ግብ በማስቆጠር ግን የተሳካላቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ነበሩ፡፡ በ43ኛው ደቂቃ መስኡድ መሀመድ ከማዕዘን ምት ያሻማት ኳስ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ጨዋታውን ማድረግ የቻለው አቡበከር ነስሩ በግንባሩ በመግጨት ቡናን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ ሲዳማ ቡና ወደ መሪነት ለመመለስ በአዲስ ግደይ አማካይነት ሁለት ያለቀላቸውን የግብ እድሎች መፍጠር ቢችልም ሳየይሳካ የመጀመርያው አጋማሽ ያለግብ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡና የእንቅስቃሴ እነና የግብ እድል የመፍጠር የበላይነቱን ሲያሳይ ወደ መሪነት ለመመለስም ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ናይጄሪያዊው አጥቂ ላኪም ሰኒ በ48ኛው ደቂቃ ፍፁም ተፈሪ በረጅሙ የሰጠውን ኳስ ከመረብ አሳርፎ ሲዳማን በድጋሚ መሪ አድርጓል፡፡

ከግቡ በኋላም ሲዳማ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንጻሩ ተቀዛቅዘው ታይተዋል፡፡ አህመድ ረሺድ በግሉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጭም የቡና የማጥቃት እንቅስቃሴ እጅግ የተገደበ ነበር፡፡

በ66ኛው ደቂቃ ሄይቲያዊው ሁለገብ ሳውሬል ኦልሪሽ ያሻማውን የማዕዘን ምት ኬንያዊው ተከላካይ ሰንደይ ሙቱኩ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ የሲዳማን ግብ ወደ ሶስት ከፍ በማድረግ መሪነቱን አስተማማኝ ማድረግ ችሏል፡፡
እያሱ ታምሩ ከመሀል ሜዳ አክርሮ የመታት ኳስ ለአለም ብርሀኑ ሲተፋው ሳሙኤል ሳኑሚ አስቆጠረ ሲባል የሲዳማ ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡበት ኳስ ምናልባትም ኢትዮጵያ ቡና ወደ ጨዋታ እንዲመለስ ምክንያት የምትሆን አጋጣሚ ናት ብሎ ከማስቀመጥ በቀር በኢትዮጵያ ቡና በኩል ውጤቱን ለመቀልበስ ያደረጉት ጥረት እምብዛም ነበር፡፡

ድሉን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 36 በማድረስ አንድ ተስተካካይ  ጨዋታ የሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመብለጥ የሊጉን መሪነት መንበር ተረክቧል፡፡ በመጪው ሰኞ አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታም ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል፡፡

Leave a Reply