ጋዲሳ መብራቴ ስለ ወቅታዊ ድንቅ አቋሙ ይናገራል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ የቻለው ሀዋሳ ከተማ ብቻ ነው፡፡ ሀዋሳ ከተማ ትላንት መከላከያን 3-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ሁለት ግብ አስቆጥሮ ጃኮ አራፋት ላስቆጠረው አንድ ግብ ጣጣውን ጨርሶ ያቀበለው ጋዲሳ መብራቴ ድንቅ እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡

ጋዲሳ መብራቴ ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያየት በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ በመሆኑ መደሰቱን ገልጿል፡፡ ” ለቡድኔ በግሌ ሁለት ጎል አስቆጥሬ አንድ ኳስ ደግሞ ለግብ አመቻችቼ በማቀበሌ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። ለዚህም በመጀመሪያ ፈጣሪን አመሰግናለሁ። በመቀጠል የቡድን ጓደኞቼን አመሰግናለሁ፡፡ የቡድን አጋሮቼ ናቸው ጥሩ እንድንቀሳቀስ ያደረጉኝ።” ያለው ጋዲሳ የውድድር ዘመን እቅዱን እያሳካ እንደሆነ ገልጿል፡፡

” በዚህ አመት በርካታ ግብ የማስቆጠር እና የተሻለ ነገር የማሣየት እቅዴን እያሳካው ነው፡፡ ግብ በማስቆጠር እና ጥሩ በመንቀሳቀስ ለጓደኞቼ የገባሁትን ቃሌን ጠብቄያለው፡፡ አሁንም በቀሪው የውድድር ዘመን የተሻለ ጊዜ ከክለቤ ጋር ማሳለፍ ተቀዳሚ አላማዬ ነው፡፡ ”

በውድድር ዘመኑ 6 ግቦች ያስቆጠረው ጋዲሳ በሊጉ የማጥቃት አጨዋዋወት ከሚጠቀሱ ቡድኖች አንዱ ለሆነው ሀዋሳ ከተማ ዋንኛ የማጥቃት መሳርያ ነው፡፡ ቡድኑ በርካታ ግቦች ቢያስቆጥርም በዛው መጠን የኋላ ክፍሉ ደካማነት ዋጋ ሲያስከፍለው ቆይቷል፡፡ በቅርብ ሳምንታት ግን ሀዋሳ የተከላካይ ክፍሉ ተረጋግቶ ወደ ውጤታማነት ተመልሷል፡፡ ጋዲሳም በዚህ መልካም ስሜት እየተሰማው እንደሆነ ገልጿል፡፡ ” ክለቡ እዚህ መገኘት ደጋፊው ቅር ብሎት ነበር፡፡ እኔም እዚህ በመገኘታችን መጥፎ ስሜት አንፀባርቆብኝ ነበር፡፡ ያ አሁን ላይ ከውስጤ ጠፍቷል፡፡ ውጤት በጠፋበት ወቅት የነበረኝ ስሜት አሁን የለም”

በዘንድሮው አመት ከሀዋሳ ጋር ያለው ኮንትራት የሚያበቃው ጋዲሳ ስለቀጣዩ ጊዜ የማሰብ ፍላጎት እንደሌለው ተናግሯል፡፡ ” አሁን ስለቀጣዩ ማውራት አልፈልግም፡፡ ጊዜው ሲደርስ አብረን ብናይ ይሻለናል፡፡ አሁን ትኩረቴ ክለቤን የተሻለ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ መርዳት እና ሀገሬን በብሔራዊ ቡድን መወከል ነው” ሲል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ ቋጭቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *