“መሪነታችንን አስጠብቀን እንደምንቀጥል እርግጠኛ ነኝ” ትርታዬ ደመቀ

ሲዳማ ቡና ትላንት በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም ከጨዋታ ብልጫ ጋር ኢትዮጵያ ቡናን 3-1 በማሸነፍ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ ነጥብ ቀድሞ የሊጉን መሪነት መረከብ ችሏል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በመጪው ሰኞ በ21ኛው ሳምንት እርስ በእርስ የሚያደርጉት ፍልሚያም የሊጉን ጉዞ ከሚወስኑ ወሳኝ ጨዋታዎች አንዱ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል፡፡ ከሲዳማ የዘንድሮው ጥንካሬ ጀርባ ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ትርታዬ ደመቀ ክለቡ የያዘውን መሪነት አስጠብቆ የመጓዝ አቅም እንዳለው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡ አማካዩ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ ብለናል፡፡

የሲዳማ ቡናን የዘንድሮ አመት ጉዞ እንዴት ታየዋለህ ?

ሲዳማ ቡና በዚህ አመት አንድ ነገር ለመስራት አስቀድመን ነበር ጠንክረን ዝግጅት ስናደርግ የነበረው፡፡ አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ እንገኛለን ፤ ከሜዳም ውጭ ነጥቦችን ይዘን እየተመለስን ነው። በአጠቃላይ እስካሁን ጥሩ ጉዞ እየተጓዝን ነው፡፡ በእርግጠኝነት ጥሩ ውጤት እናስመዘግባለን ብዬ ነው የማስበው።

ሲዳማ ቡናን ዘንድሮ ነው የተቀላቀልከው ፤ በፍጥነትም ከቡድኑ ጋር ተላምድሀል…

ለቡድኑ አዲስ ነኝ ብዬ ብዙ ትኩረት አልሰጠሁትም፡፡ በፍጥነት ከቡድኑ ጋር እንደምላመድ አስቤ ነው ወደ ሲዳማ ቡና የመጣሁት፡፡ ምክንያቱም እግር ኳስ ተጨዋች ከሆንክ የትም ሄደህ በፍጥነት በመላመድ መጫወት አለብህ፡፡ ሌላው በአርባምንጭ አብረውኝ የተጫወቱ ተጫዋቾች ስለነበሩ ለመላመድ አልቸገረኝም።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን ለሲዳማ ቡና ጥሩ ጉዞ ጎል በማስቆጠር ጎል የሚሆኑ እድሎችን በመፍጠር በግልህ ጥሩ አስተዋፅኦ እያበረከትክ ነው፡፡ ይህን እንዴት ታየዋለህ?

ያው ከልጅነት ጀምሮ ብዙ ስሰራበት የመጣሁት ስለሆነ ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላም ብዙ የምሰራው የቤት ስራ አለብኝ፡፡ እስካሁን ባለው ነገር ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን ጥሩ የውድድር አመት እያሳለፍኩ እገኛለው፡፡ ከዚህም በኋላም ጥሩ ነገር እሰራለው ብዬ አስባለው ።

አሁን በሊጉ መሪ መሆን ችላችኋል፡፡ ከዚህ በኋላ ከሲዳማ ቡና ምን እንጠብቅ ?

በግሌም ሆነ ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን ጥሩ ነገር እየሰራን እንገኛለን ፤ ከዚህ በኋላም ለመስራት እናስባለን፡፡ አሁን የሊጉ መሪ መሆን ችለናል፡፡ ይህን አስጠብቀን እንደምንቀጥል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከፊት ለፊታችን ሰኞ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ወሳኝ ጨዋታ በማሸነፍ ነጥብ ከያዝን በእርግጠኝነት ማንም ሊይዘን አይችልም። የቡድን አጋሮቼም ላይ ጥሩ የመነቃቃት መንፈስ አለ፡፡ አሰልጣኞቻችን ጥሩ ነገር እየሰጡን ነው ፤ የቡድኑ አመራሮችም ተገቢውን ድጋፍ እያደረጉልን ስለ ሆነ ዘንድሮ ጥሩ ነገር እናደርጋለን ብዬ አስባለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *